(ኢሳት ዜና– ነሐሴ 4/2009) በሌብነት ወንጀል የተጠረጠሩ የ210 ግለሰቦችና ተቋማት ንብረት መታገዱን መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
የታሰሩት ግለሰቦች 54 ሲሆኑ የታገደው የ210 ግለሰቦችና ተቋማት ንብረት መሆኑ ተጨማሪ የሚታሰሩ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን የሚጠቁም ሆኗል።
የተጠርጣሪዎቹና ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ንብረታቸው ከታገደው ውስጥ በከፊሉን የሕወሃት ንብረት የሆነው ሬዲዮ ፋና ይፋ አድርጓል።
በዚህም አሰር ኮንስትራክሽኝ፣ግምሹ በየነ ኮንስትራክሽን፣ቲና ኮንስትራክሽን፣ዲ ኤም ሲ ኮንስትራክሽን፣የማነ ግርማይ ጠቅላላ ስራ ተቋራጭ ከታገዱት ውስጥ ተዘርዝረዋል።
እንዲሁም ትራንስ ናሽናል ኮምፒውተር ትሬዲንግ፣ ሀይሰም ኢንጂነሪንግ አክሲዮን ማህበር፣ ከማኒክ ትሬዲንግ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ጆንግ ሊንግ ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ እና ሌሎችም ይገኙበታል።
ከተዘረዘሩት ውስጥ አንዱ የሆነው ገምሹ በየነ ኮንስትራክሽኝ የኢሊሊ ሆቴል ባለቤት የአቶ ገምሹ በየነ እንደሆነም ታውቋል።