(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 2/2009)የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ም/ሊቀመንበር የአቶ በቀለ ገርባ የዋስትና ጥያቄ በአንድ ወር ለ6ኛ ግዜ ተቀጠረ።
ፍርድ ቤቱ ብይኑን ዳኞች አልተሟሉም፣ዳኞች ታመዋል በሚል በማራዘም ላይ መሆኑም ታውቋል።
የተመሰረተባቸው የአሸባሪነት ክስ ዝቅ ብሎ ጉዳያቸው በወንጀል ክስ እንዲታይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያሳለፈው ከሶስት ሳምንት በፊት ቢሆንም የዋስትና ጥያቄያቸው ምላሽ ሳያገኝ ለ6ኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ተመልክቷል።
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ በኦሮሚያ ክልል የተቀጣጠለውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ ከ20 ወራት በፊት ለሁለተኛ ጊዜ መታሰራቸው ይታወቃል።
አመጹን በማነሳሳትም በአሸባሪነት ተወንጅለው ከሌሎች የኦፌኮ አመራሮች ጋር ወደ ወህኒ የተጋዙት አቶ በቀለ ገርባ ሐምሌ 6/2009 የቀረበባቸው ክስ ከአሸባሪነት ወደ ወንጀል ክስ ዝቅ እንዲል በፍርድ ቤት ተወስኗል።
በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት በተሰጠው ብይን መሰረትም የተሻሻለው ክስ ዋስትና የማይከለክል በመሆኑ አቶ በቀለ ገርባ በጠበቆቻቸው አማካኝነት የዋስትና ጥያቄ ያቀረቡት ወዲያውኑ ቢሆንም ችሎቱ በጉዳዩ ላይ ብይን ለመስጠት 5 ጊዜ የሰጠው ቀጠሮ የተለያዩ ምክንያቶች እየቀረቡበት ተስተጓጉሏል።
ዳኞች አልተሟሉም ፣ወይንም ከዳኞቹ አንዱ ታሟል በሚል ለአምስት ጊዜ ሲገፋ የቆየው ውሳኔ ዛሬ ነሀሴ 2/2009 ደግሞ ተመሳሳይ ምክንያት ተሰጥቶት ለ 6ኛ ግዜ ለቀጣዩ ሳምንት ተቀጥሯል።
ፍርድ ቤቱ ወይንም ማረሚያ ቤቱ አልያም ሁለቱም በጋራ የተለየ ምክንያት ካልሰጡ የአቶ በቀለ ገርባ የዋስትና ጥያቄ በቀጣዩ ሳምንት ሀሙስ ነሀሴ 11/2009 ውሳኔ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ በቅድሚያ በ2003 በተመሳሳይ በቀረበባቸው ክስ ለ5 አመታት ያህል ወህኒ ቆይተው በተፈቱ በወራት ልዩነት ተመልሰው መታሰራቸው ይታወሳል።