(ኢሳት ዜና– ነሐሴ 2/2009)በደብረታቦር ከተማ የተጀመረው አድማ ቀጥሎ መዋሉ ታወቀ።
በከተማዋ ሁሉም መደብሮች እንደተዘጉ ናቸው።
የአካባቢው ባለስልጣናት በከተማዋ እየዞሩ የንግድ ተቋማትን ማሸጋቸውንም ያገኘንው የምስልና የቪዲዮ ማስረጃ ያመለክታል።
በደብረታቦር፣በወረታ፣በወልዲያና በተለያዩ አዋሳኝ አቅራቢያዎች የተመታው የህዝብ አድማ ሰበቡ ከግብር ጋር የተያያዘ ቢሆንም አጠቃላይ ምክንያቱ ግን በአገዛዙ መማረርና የአስተዳደር በደል ነው።
በተለይ በደብረታቦር ህዝቡ እየደረሰበት ያለው ችግር ከትእግስት በላይ እንደሆነበት የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ይህንኑ ተከትሎም በደብረታቦር አጠቃላይ የስራ ማቆም አድማ እየተደረገ ይገኛል።በደብረታቦር የንግድ መደብሮች ሙሉ በሙሉ እንደተዘጉ ናቸው።
በህዝቡ አንድ መሆን ግራ የተጋቡት የአገዛዙ ባለስልጣናትም የሚያደርጉት ቢያጡ እየዞሩ የንግድ መደብሮችን እያሸጉ መሆናቸው ተነግሯል።
ሕብረተሰቡ ግን በካድሬ ባለስልጣናት ርምጃ አልተደናገጡም ነው የተባለው።
አንድ አስተያየት ሰጪ እነሱ በራችን ላይ ወረቀት ቢለጥፉም መደብራችንን ግን ቀድመን ያሸግንው እኛ ነን ይላሉ።
ስለዚህም በግብር ስም የሚደርስብን በደልና ሌሎች አስተዳደራዊ ችግሮች እስካልተወገዱ ድረስ ትግላችንን እንቀጥላለን ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል።
በደብረታቦር የተመታው አድማ በወልድያም ተደግሟል።ወረታ፣ጎንደር እንዲሁም በምስራቅ ጎጃም የተወሰኑ ከተሞች ተመሳሳይ ተቃውሞዎች እንዳሉ ነው የተነገረው።
በአዊ ዞን፣በኮሶበርና አጎራባች ወረዳዎች አድማው መኖሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
ሁሉም አድማውን ያደረጉ የየከተሞቹ ነዋሪዎች የሚስማሙበት አንድ ጉዳይ አለ።ይህም አገዛዙ ሕዝቡን ማስመረሩን እንዲያቆም ብሎም ስልጣኑን መልቀቅና የተሻለ ስርአት መፈጠር አለበት የሚል ነው።