(ኢሳት ዜና –ነሐሴ 1/2009) የአምቦና የወሊሶ ነዋሪዎች ዶክተር መራራ ጉዲናን ጨምሮ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ በመጠየቅ የስራ ማቆም አድማ አደረጉ።
በአምቦ ተሽከርካሪዎችና የንግድ መደብሮች ሙሉ በሙሉ ተዘግተው መዋላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የስራ ማቆም አድማው ለተከታታይ ቀናት ይቀጥላል ተብሏል።
በአምቦና ወሊሶ እንዲሁም በአካባቢዎቹ የተጀመረው የስራ ማቆም አድማ ዶክተር መራራ ጉዲናና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅ ነው።
ዶክተር መራራና አቶ በቀለ ገርባና ሌሎችም የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አባላትና የፖለቲካ እስረኞች ያለቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
የአምቦና የወሊሶ ነዋሪዎች ከግብር ጋር በተያያዘም ተቃውሞአቸውን እያሰሙ መሆናቸውንም ምንጮቹ ገልጸዋል።
በዶክተር መራራ ጉዲና የእስር አያያዝም ተበሳጭተናል ያሉት የአምቦና የወሊሶ ከተማ ነዋሪዎች አገዛዙ እኒህን አንጋፋ ምሁር በአስቸኳይ እንዲለቅ ጠይቀዋል።
በአምቦ ዛሬ በጀመረው አድማ ሱቆች፣ሆቴሎችና የንግድ መደብሮች ተዘግተው ውለዋል።
የትራንስፖርት አገልግሎትም ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል።ከአድማው ጋር በተያያዘ ባንኮችና የኢትዮጵያ ሆቴል ለመተባበር ዝግጁ አለመሆናቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል።
እናም በተቋማቱ ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደዱም የአካባቢው ወጣቶች ዝተዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታም በደቡብ ምእራብ ሸዋ ወሊሶ አድማው እየተካሄደ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የወሊሶ ህዝብ የዶክተር መራራን እስርና የስቃይ አያያዝ በመቃወም ሰልፍ ለማካሄድ እየተዘጋጀ መሆኑ ነው የተነገረው።
በአምቦና ወሊሶ የአገዛዙ ሃይሎች አድማውን ለማስቀረት እየተሯሯጡ መሆኑንም ያገኘንው መረጃ ያመለክታል።