(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 1/2009)በኦሮሚያ ክልል ሞጆ ከተማ የቻይናውያን ንብረት የሆነው የቆዳ ፋብሪካ የሚያደርሰውን ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት የተቃወመው የሰራተኛ ማሕበር ሊቀመንበር ከስራ ታገደ።
አንዲት ሰራተኛ ሁለት እጆቿን ሙሉ ለሙሉ ስታጣ፣ከስምንት በላይ ሰራተኞች ደግሞ ከፍተኛ አደጋ ደርሶባቸዋል።
ከአምስት አመት በፊት ተገንብቶ ወደ ስራ የገባውና ከ1500 በላይ ሰራተኞች ያሉት ይህ የቆዳ ፋብሪካ ለሰራተኞች የደህንነት ጥበቃ የሚያደርጉ አሰራሮችንም ሆነ ቁሳቁሶችን ማሟላት አልቻለም በዚህም የፋብሪካው ሰራተኞች አደጋ ላይ ወድቀዋል ሲል የሰራተኛ ማህበሩ ሊቀመንበር አጋልጧል።
ሊቀመንበሩ አቶ አታኪአ ኢዶ በሰራተኛው ላይ እየደረሰ ያለውን አደጋ ለምን አጋለጥክ በሚልም በአስተዳደር ውሳኔ ከስራው እንዲታገድ ተደርጓል።–ይህ ውሳኔም አግባብነት የሌለው ነው ሲል አቶ አታኪአ ተቃውሞውን አሰምቷል።
ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከስምንት በላይ ሰራተኞች በእጆቻቸው ላይ ከፍተኛ አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን አንዲት ሰራተኛ ሁለት እጆቿ ሙሉ ለሙሉ በማሽን መቆረጣቸውን የሰራተኛ ማህበሩ ለኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበር ኮንፌዴሬሽን ባስገባው ደብዳቤ ሪፖርተር ጋዜጣ በእንግሊዘኛ እትሙ አስታውቋል።
በቀን ከአርባ ብር በታች እየተከፈላቸው በከፍተኛ የደህንነት ስጋት ውስጥ የሚሰሩት የፋብሪካው ሰራተኞች አቤቱታቸውን ለከተማው አስተዳደር ቢያቀርቡም እስካሁን ምንም አይነት ምልሽ ማግኘት አለመቻላቸውም ተገልጿል።