(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 28/2009)ከመስከረም 28/2009 ጀምሮ ላለፉት 10 ወራት ተግባራዊ ሆኖ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዛሬ መነሳቱ ተገለጸ።
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳም በየክልሉ ሙሉ ስልጣን ተሰጥቶት የተሰማራው ኮማንድ ፖስት ስራውን እንደሚቀጥል በፓርላማው ይፋ ሆኗል።
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነሳ ተብሎ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስራውን የጀመረው ኮማንድ ፖስት አለመፍረሱ አነጋጋሪ ሆኗል።
ይህም መንግስት ከኢንቨስትመንትና ከቱሪዝም ጋር በተያያዘ የገጠመውን ቀውስ ለመሻገር ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እይታ ሲባል ብቻ በቃል የተነሳ በድርጊት የቀጠለ እንደሆነም ታምኖበታል።
ሰኔ 30/2009 እረፍት በወጣውና በመስከረም 2010 መጨረሻ መመለስ የሚጠበቅበት ፓርላማ ድንገት አስቸኳይ ስብሰባ መጠራቱ የተሰማው በሳምንቱ መጀመሪያ ነበር።
ፓርላማው መጠራቱን ባለፈው ረቡእ ማረጋገጫ የሰጡት የፓርላማው የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ጸዳለ ረጋሳ ለምን እንደተጠራ እንደማያውቁ መናገራቸው ይታወሳል።
ፓርላማው ዛሬ አርብ ሐምሌ 28/2009 የጠራው አስቸኳይ ስብሰባ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ለመምከር እንዲሁም የተጓደሉ የካቢኔ አባላትን ለመተካትና በሌብነት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ያለምከሰስ መብት ለማንሳት እንደሆነም ታውቋል።
በዚህም መሰረት የእስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሴክሬቲሪያት አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ባቀረቡት ሪፖርት መሰረትም ፓርላማው አስቸኳይ ግዜ አዋጁን እንዳነሳ ተዘግቧል።
አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት ለአዋጁ መነሻ የሆኑ ችግሮች በአንዳንድ አካባቢዎች መቀጠላቸውን አረጋግጠዋል።
ሆኖም በመደበኛው የህግ አግባብ ለማስተናገድ ሲባል አዋጁ እንዲነሳ መወሰኑን ለፓርላማው ገልጸዋል።
ችግሮቹ የቀጠሉባቸውን አካባቢዎች ግን ይፋ አላደረጉም።
ፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዳነሳ ቢገልጽም በአዋጁ መሰረት የተቋቋመውና በክልሎች በበላይነት ጸጥታውን የሚቆጣጠርው ኮማንድ ፖስት እንዳልፈረሰ ታውቋል።
ይህ ሃይል ከክልል ሃይሎች ጋር ጸጥታውን እንዲቆጣጠር መወሰኑም ተመልክቷል።
ኮማንድ ፖስቱ ባልፈረሰበት ሁኔታ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነሳ ለማለት ያስቸግራል የሚሉት የፖለቲካ ተንታኞች አላማው በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ዘርፍ የተከሰተው ችግር ያባባሰውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመሻገር ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ፍጆታ ሲባል በቃል የተነሳ በድርጊት የቀጠለ ሲሉ ይገልጹታል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ አሁንም ወደ 8 ሺ ሰዎች በወህኒ ቤት እንደሚገኙ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት አመልክተዋል።
በኦሮሚያ ክልል 4 ሺ 136 ሰዎች በወህኒ ሆነው ክስ ሲመሰረትባቸው፣ በአማራ ክልል ደግሞ 1 ሺ 166 እንዲሁም በአዲስ አበባ 547 ሰዎች እስር ቤት ሆነው ክስ ተመስርቶባቸዋል።
በአጠቃላይ 7 ሺ 737 ሰዎች በወህኒ እንደሚገኙም አረጋግጠዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከኦሮሚያ፣ከአማራ፣ደከቡብ ክልሎችና ከአዲስ አበባ ውጭ የታሰረ እንዳለም ተመልክቷል።
በአማራ ክልል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ታስረው በወህኒ ቤት ከሚገኙት ውስጥ በአርቲስት ፋሲል ደሞዝ ዘፈን ጨፍራኋል በሚል የታሰሩ ወጣቶች ይገኙበታል።
ህዳር 21/2009 በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 05 ልዩ ስሙ ማሬ ተመስገን አረቄ ቤት ውስጥ የፋሲል ደሞዝን ሒድልኝ የሚለውን ዘፈን በሞባይል ስልካቸው ከፍተው ጨፍረዋል በሚል ተይዘው የታሰሩትና የተከሰሱት እንዳልክ ስራውቀና፣ ተመስገን ሞገስና ሰለሞን ግርማ የተባሉ የ17 የ18ና የ20 አመት ወጣቶች መሆናቸውን ከአቃቢ ህግ የክስ መዝገብ ለማወቅ ተችሏል።