(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 27/2009) በኢትዮጵያ ከሴቶች ወሊድ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ አገልግሎት የሰጡት ዶክተር ካትሪን ሐምሊን የተባበሩት መንግስታት የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ተደረጉ።
ሽልማቱ የተሰጠው የተባበሩት መንግስታትን እሴቶች በበጎ ላስተዋወቁ አውስትራላውያን እውቅና በሚሰጠው ተቋም አማካኝነት ነው።
ዶክተር ካትሪን ሐምሊን የሕይወት ዘመናቸውን በኢትዮጵያ ለፌስቱላ የተጋለጡ 50ሺ ሴቶችን በመታደግ አገልግሎት የሰጡ አውስትራሊያዊ ሀኪም ናቸው
ዶክተር ሐምሊን እድሜ ልካቸውን ከባለቤታቸው ጋር በመሆን በፌስቱላ የሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያንን በመርዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ አንጋፋ ሀኪም ናቸው።
ባለቤታቸው ዶክተር ሀምሊንም በተመሳሳይ ሁኔታ ከጎናቸው በመቆም ለኢትዮጵያ ሴቶች ጤና የበኩላቸውን ሲያደርጉ ኖረዋል።–በልጅነታቸው በመውለዳቸው ሳቢያ ለፌስቱላ ህመም የተዳረጉ ሴቶችን በማከምና በማገዝ
ዶክተር ካትሪን ሐምሊን በኢትዮጵያ የፌስቱላን በሽታ የማስወገድ ሕልም አላቸው።
እስካሁን በነበራው አገልግሎታቸውም 50 ሺ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ከፌስቱላ በሽታ ታድገዋል።
እናም ይህን አገልግሎታቸውን የተገነዘበው የተባበሩት መንግስታት የአውስትራሊያ ማህበር የተባለው ተቋም የ2017 የሕይወት ዘመን ተሸላሚ አድርጎ መርጧቸዋል።
ተቋሙ ለፍትህ፣ ለሰላምና በዝቅተኛ ደረጃ ላሉ የማህበረሰብ አባላት ለሰሩ አውስትራላውያን እውቅና በመስጠት ተሸላሚ ያደርጋል።
በዚሁ መሰረት ላለፉት 60 አመታት በኢትዮጵያ ከወሊድ ጋር በተያያዘ ለፌስቱላ በሽታ የተጋለጡ ሴቶችን በማከምና እገዛ በማድረግ አገልግሎት ለሰጡት ዶክተር ካትሪን ሐምሊን ሽልማቱን አብርክቶላቸዋል።
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በያዝነው ወር መጨረሻ ለሽልማት የበቁት ዶክተር ሐምሊን ኑሯቸው በኢትዮጵያ በመሆኑ በተወካያቸው አማካኝነት የእውቅና ስነ ስርአቱ እንደተዘጋጀላቸው ተገልጿል።
ዶክተር ካትሪን ሐምሊን በኢትዮጵያ የፌስቱላ ሆስፒታል ገንብተው በአለም ደረጃ ከፍተኝ እውቅና ያለው በጎ አገልግሎታቸውን አሁንም በ93 አመት እድሜያቸው እየሰጡ ይገኛሉ።