(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 26/2009)በሰሜን ሸዋ ሸዋሮቢት ነጋዴው የመታውን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ ስብሰባ ተጠርቷል። በስብሰባው ላይ ግን የከተማዋ ከንቲባና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት መስማማት አልቻሉም።ነጋዴዎቹም የጀመሩትን አድማ እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
በአማራ ክልል በአብዛኛው አካባቢ የግብር ተመኑ ይፋ ሆኗል። ይህን ተከትሎም አድማ ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ስጋት በመንግስት ዘንድ ተፈጥሯል።
የንግዱ ማህበረሰብ በአንድነት ቅሬታውን እንዳያሰማና በተቃውሞ እንዳይነሳ በመንግስት በኩል ከተወሰዱት ርምጃዎች አንዱ የተጣለውን የግብር ተመን ከፋፍሎ ይፋ ማድረግ ነበር።
በተለይም በአማራው ክልል በአንድ ከተማ የሚገኙ ነጋዴዎች ሳይቀር የግብር ተመኑ እንዲደርሳቸው የተደረገው በተለያዩ ጊዜያት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህም የተባበረ የህዝብ ሃይል ፈንቅሎ እንዳይወጣ ከሚል ስጋት ሲሆን በተወሰነ ደረጃ በአንዳንድ ከተሞች ለተቀዛቀዘው የአድማ እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ ማድረጉ ተገልጿል።
ዛሬ ግን በአማራ ክልል በአብዛኛው አካባቢ የግብር ተመኑ ይፋ መደረጉ ታውቋል።በዚህም መሰረት ከደረጃ ሐ ወደ ደረጃ ለናሀ የተሻገሩ ነጋዴዎች ዝርዝር ተገልጿል።
አንዳንዱ ነጋዴ የግብር ደረጃውንና የሚከፍለውን የገንዘብ መጠን የሚገልጽ ደብዳቤ እንዲደርሰው እየተደረገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
አሰራሩ ፖለቲካዊ ወገንተኝነት የታየበት የስርአቱ አባልና ደጋፊ የሆኑ ነጋዴዎችን እየጠቀመ አብዛኛውን የነጋዴውን ክፍል ከጨዋታ ውጪ የሚያደርግ መሆኑንም ይናገራሉ።
አብዛኞቹ ወደ ደረጃ ሐ ዝቅ እንዲሉና አነስተኛ ግብር እንዲከፍሉ የተደረጉት ስልጣን ላይ ላለው ስርአት ቅርበት ያላቸው ነጋዴዎች ናቸው ሲል የኢሳት የመረጃ ምንጭ ገልጿል።
በባህር ዳር ከ1ሺ በላይ ነጋዴዎች ከደረጃ ሐ ወደ ደረጃ ለናሀ ከፍ እንዲሉ መደረጋቸው ታውቋል።
በሌሎች ከተሞችም በተመሳሳይ በሺዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች ላይ የግብር ተመኑ በአምስትና አራት እጥፍ መጨመሩን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል በሰሜን ሸዋ ሸዋሮቢት የተጀመረው የነጋዴዎች የስራ ማቆም አድማ ለሶስተኛ ቀን በቀጠለበት በዛሬው እለት የመንግስት ሃላፊዎች የንግዱን ማህበረሰብ መሰብሰባቸው ታውቋል።
የከተማው ከንቲባ በትላንትናው እለት ቤት ለቤት እየዞሩ ማስፈራራታቸውን ተከትሎ በቁጣ ላይ የነበረው ማህበረሰብ ስብሰባውን እንደጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም ተቃውሞውን ማሰማቱን ነው ከስፍራው ያነጋገርናቸው የገለጹልን።
የአድማው እንቅስቃሴ ከተጀመረ አንስቶ በታጠቀ ሰራዊት የተከበበችው ሸዋሮቢት ዛሬም በስብሰባው ቦታ በርከት ያሉ የፌደራልና የልዩ ሃይል ሰራዊት አባላት የህዝቡን ስነ ልቦና ለማሸበር ሲንቀሳቀሱ ነበር ተብሏል።
አዋረዳችሁን፣ ገጽታችንን አበላሻችሁ፣አስችኳይ ጊዜ አዋጁን ጣሳችሁ ብለው በቁጣ ንግግራቸውን ለጀመሩት ከንቲባ ህዝቡ አንፈራችሁም፣ ግብሩንም አንከፍልም በሚል በአንድ ድምጽ ምላሽ መስጠቱን በስብሰባው ላይ የነበሩ አንድ ግለሰብ ለኢሳት ገልጸዋል።
የሸዋሮቢት ስብሰባ ያለውጤት ተበትኗል።ከስርአቱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ነጋዴዎች የተወሰኑት ዛሬ ሱቆቻቸውን መክፈታቸው የተገለጸ ሲሆን ህዝቡ መልእክት እየላከባቸው መሆኑ ታውቋል።
ዛሬም በርካታ ሱቆችና መደብሮች እንደተዘጉ ናቸው።ሐምሌ 30 የግብር ክፍያው የጊዜ ገደብ የሚያበቃበት ቀን እሁድ ደርሷል።የሸዋ ሮቢት ነጋዴዎች ከግብር እንከፍልም ተቃውሞ ተሻግረው የስርአት ለውጥ እያነሱ እንደሆነም ይነገራል።