(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 26/2009)የቴሌኮም ማስፋፊያዎችን ከኢትዮ-ቴሌኮም በመውሰድ የሚሰራው ኤሪክሰን ኩባንያ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ መግባቱ ተገለጸ።
የስዊዲን ኩባንያ የሆነው ኤሪክሰን በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የቴሌኮም ማስፋፊያ አራት ፕሮጀክቶችን በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2014 በመፈራረም ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።
ባጋጠመው የአለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ችግርና የትርፍ ማጣት ምክንያትም ከፍተኛ አደጋ ውስጥ መግባቱን ለኢሳት የደረሰው መረጃ አመልክቷል።
ኤሪክሰን ከተረከባቸው አራት ፕሮጀክቶች መካከል በደቡብና ደቡብ ምእራብ አካባቢዎች በሚገኙት አርባምንጭ፣ወላይታ ሶዶና የአካባቢ ከተሞች የሚያካሂዳቸው የ3ጂ ኔትወርክ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን በወቅቱ ማጠናቀቅ ባለመቻሉ ምክንያት ስምምነቱ ከአንድ አመት በፊት እንዲቋረጥ ተደርጓል።
ፕሮጀክቶቹም ከኤሪክሰን ተነጥቀው ለቻይናው ኩባንያ ህዋዌ መሰጠቱ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
ኤሪክሰን ባለፉት ወራት በሐዋሳና ዙሪያዋ ባሉ ከተሞች የተረከበውን ፕሮጀክቶች አጠናቅቄያለሁ ቢልም የኔትወርክ ዝርጋታው፣የኢንተርኔት ፍጥነቱ ደካማ መሆንና ዲጂታል ምስሎችን ማስተላለፍ አለመቻሉ ከተጠቃሚዎች ቅሬታ ማስነሳቱን የአካባቢው የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የአለም አቀፍ የሚዲያ ተቋም የሆነው ሮይተርስ የኤሪክሰን የትርፍ መጠን ከ94 በመቶ መቀነሱንና የሽያጭ መጠኑም ከ14 በመቶ በታች ማሽቆልቆሉን መዘገቡ የሚታወስ ነው።