(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 25/2009)በግብር ተመን የተነሳ በመላ ሀገሪቱ እየተደረገ ያለው ተቃውሞ መቀጠሉን ከተለያዩ አካባቢዎች የሚደርሱ መረጃዎች አመለከቱ።
ምስራቅ ጎጃም በበርካታ ከተሞች የስራ ማቆም አድማው እንደቀጠለ ነው።
አዳዲስ ከተሞችም በመቀላቀላ ላይ ናቸው።በሰሜን ጎንደር ዳባርቅም ዛሬ የአድማ ርምጃ ተወስዷል።የስራ ማቆም አድማ በተደረገባቸው ከተሞች የስርአቱ ወታደሮችና የፖሊስ ሃይል መሰማራታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ነጋዴው ማህበረሰብ አንድ ላይ እንዳይነሳ የግብር ተመኑን እየነጣጠሉ እንዲደርስ ማድረጋቸው እየተገለጸ ነው።
በግብር ተመን የተነሳ በመላ ሀገሪቱ እየተደረገ ያለው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው
ምስራቅ ጎጃም በአድማው ገፍቶበታል።ከትልልቆቹ ከተሞች እስከ አነስተኛ የገጠር ቀበሌ መንደር ድረስ የአድማው እንቅስቃሴ የወረርሽኝ ያህል ተዛምቷል።ሞጣ፣ደብረማርቆስ፣ሉማሜ፣ፍኖተ ሰላም፣ቡሬ፣ደብረወርቅ፣ብቸና፣በከፊልም ሙሉ በሙሉም አድማ የመቱ ሲሆን ሱቆች ተዘግተዋል የንግድ ቦታዎች ከእንቅስቃሴ ውጪ ሆነዋል።
በደብረማርቆስና በደምበጫ ለ3 ቀናት የተጠራው የስራ ማቆም አድማ የቀጠለ ሲሆን የስርአቱ ወታደሮች ነጋዴውን ማህበረሰብ በማዋከብ ላይ መሆናቸውን ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በደብረማርቆስ ያዝ ለቀቅ አድርጎ የዘለቀው የአድማ እንቅስቃሴ ከትላንት ጀምሮ አብዛኛውን የንግድ አካባቢ በማካተት የቀጠለ ሲሆን የስርአቱ አመራሮች አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል።
በአድማ ላይ የሚገኙት ነጋዴዎች ግን ስብሰባውን እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል።
በጎንደር ተመሳሳይ የነጋዴዎች የስራ ማቆም አድማና ፈቃድ የመመለስ እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑ ታውቋል።በሰሜን ጎንደር ደባርቅ ዳባት በደቡብ ጎንደር ወረታ ደብረታቦር የስራ ማቆም አድማ በከፊል መጀመሩ ታውቋል።
በደባርቅ ከተማ በቅሎና መኪና ለቱሪስቶች በማከራየት ገቢ የሚያገኙ ነዋሪዎች የቀን ገቢ ግብር መክፈል አለባችሁ የሚለው ደብዳቤ ከተመኑ ጋር ከደረሳቸው ከትላንት ጀምሮ ስራ እንዳቆሙ ተገልጿል።በአማራ ክልል በተካሄደው ህዝባዊ እምቢተኝነት የተነሳ የተዳከመው የቱሪስቶች እንቅስቃሴ በአድማው ምክንያት የበለጠ እየተዳከመ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በወረታ ከተማም የአድማ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።የተጣለብን ግብር አግባብ አይደለም ቅሬታችንን የሚሰማ አካል ባለመኖሩ የስርአት ለውጥ እንፈልጋለን የሚለው አቋም በወረታ ነጋዴዎች እየተንጸባረቀ እንደሆነ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በደባርቅ፣ዳባት፣ወረታና ደብረታቦር እየታየ ያለው እንቅስቃሴ መንግስትን ስጋት ውስጥ እንደከተተውም ይነገራል።
በወሎ አጅባር የተጀመረው አድማ ነገ ሳምንቱን ይደፍናል። ሱቆች ታሽገዋል። በአድማው የተሳተፉትን በሃይል ለማስቆም በስርዓቱ ሃይሎች የተደረገው ጥረት አልተሳካም ተብሏል።
በደሴ በአንዳንድ የንግድ ቦታዎች የአድማ እንቅስቃሴ መታየቱን ተከትሎ፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደር መሰማራቱ ታውቋል።
የመንግስት ካድሬዎች ቤት ለቤት እየዞሩ የንግድ ቤቶችን ማሸግ መጀመራቸው፡ የተገለጸ ሲሆን፡ አንዳንድ ነጋዴዎችን በማሰር የተጀመረውን እንቅስቃሴ ለማስቆም ጥረት እየተደረገ ነው። በሰሜን ሸዋ የሸዋ ሮቢት ከተማ በአድማ 3ኛ ቀኗን ይዛለች። ንግድ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል። ህዝቡ አጠቃላይ የስርዓት ለውጥ ጥያቄ እያነሳ ነው።
ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የሚመራው መንግስት ነጋዴው በአንድነት ይነሳል በሚል ስጋት የግብር ተመኑን እየከፋፈለ በማሳወቅ ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ።በክልሎች ለተወሰኑት ሲያሳውቅ ለተቀሩት እስካሁን የሚከፍሉት የግብር መጠን እንዳልደረሳቸው ታውቋል።
ይህ አይነቱ ስትራቴጂ ህዝቡ በአንድነት እንዳይነሳ የታቀደ የመረጃ ምንጮች ያሳያሉ።ዛሬ በባህር ዳር ፣አዴት፣በአዊ፣በዳንግላና በቻግኒ ከተሞች በከፊል እየነጣጠሉ የግብር ውሳኔ ተመን እያሳወቁ እንደሆነም ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
በእንዲህ አይነቱ ከፋፋይና ነጋዴውን የሚነጣጥል አሰራርን ህዝቡ ነቅቶ መከታተልና አብሮ መነሳት እንደሚገባው መልእክቶች ከተለያዩ አካባቢዎች እየተላኩ ነው።
አድማ እየተደረገባቸው ባሉ ከተሞች ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ የሚመራው መንግስት በከፍተኛ ቁጥር ሰራዊቱን ማሰማራቱን ከተለያዩ ቦታዎች የሚደረሱን መረጃዎች አመልክተዋል።
በደባርቅ የልዩ ሃይልን ዩኒፎርም የለበሱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በብዛት ተሰማርተዋል።
በባህርዳር ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በከተማዋ ጎዳናዎች በመዘዋወር ሲያስፈራሩ እንደነበርም ታውቋል። ትላንት በሸዋ ሮቢት በተመሳሳይ በኦራል ተሽከርካሪዎች የተጫኑ ወታደሮች ህዝቡን ሲያዋክቡት መዋላቸውን ከአካባቢው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።