(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 25/2009)የቀድሞው የመኢአድ ሊቀመንበር አቶ ማሙሸት አማረ የአሸባሪነት ክስ ተመሰረተባቸው።
አቶ ማሙሸት አማረ የጎንደርንና የጎጃምን አመጽ በማስተባበር እንዲሁም በሰሜን ሸዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በማቋቋም ተወንጅለዋል።
የአሸባሪነት ክስ የተመሰረተባቸው አቶ ማሙሸት አማረ ከመአሕድ ምስረታ ጀምሮ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የቆዩና በኋላም በመኢአድና ቅንጅት ውስጥ በማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ማክሰኞ ሐምሌ 25/2009 የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ማሙሸት አማረ በኦሮሚያ ክልል የነበረው ሕዝባዊ እምቢተኝነት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲስፋፋ አባላትን መልምለሃል በሚል ተወንጅለዋል።
በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ ግለሰቦች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የጎንደሩንና የጎጃሙን ህዝባዊ አመጽ በማስተባበር ክስ የቀረበባቸው አቶ ማሙሸት አማረ ለግንቦት ሰባት አባላትን በመመልመልና ወደ ኤርትራ በመላክ እንዲሁም በሰሜን ሸዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በመመስረትም ክስ ቀርቦባቸዋል።
በወህኒ ቤት የሚገኙት አቶ ማሙሸት አማረ ለነሐሴ 1/2009 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ወደ እስር ቤት መመለሳቸውም ታውቋል።
የቀድሞው የመኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት አማረ አይ ሲስ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጸመውን ዘግናኝ ግድያ ለመቃወም መንግስት ሚያዚያ 14/2007 የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ወደ ጸረ መንግስት ተቃውሞ ቀይረሃል በሚል ተከሰው ታስረው ነበር።
ሆኖም በእለቱ በስፍራው እንዳልነበሩ በመረጋገጡ በፍርድ ቤት ተፈተዋል።
ባለፉት 26 አመታት በፖለቲካ ትግል ውስጥ የቆዩት አቶ ማሙሸት አማረ የደብረብርሃን ወሕኒ ቤትን በመስበር እንዲሁም ከቅንጅት አመራሮች ጋር ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በሃይል ለመናድ በሚል የተመሰረተባቸውን ክስ ጨምሮ በአጠቃላይ ለ10 ጊዜያት ያህል መታሰራቸውም ተመልክቷል።
አቶ ማሙሸት አማረ በሚያደርጉት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከታሰሩት ውስጥ ከታዋቂው የሕክምና ባለሙያና የመአህድ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አስራት ጋር ወደ 8 አመታት በወህኒ ማሳለፋቸውን የቅርብ ምንጮች ያስታውሳሉ።
አቶ ማሙሸት አማረ ከተከሰሱባቸው ክሶች አንዱ የሆነው የደብረብርሃን ወህኒ ቤት ሰበራ ባለፉት 26 አመታት ከተከሰቱ የተቃውሞ ድርጊቶች አንዱ እንደነበርም ማስታወስ ተችሏል።
ከ650 በላይ እስረኞችን ማስመለጥ የተቻለበትና ደብረብርሃን ከተማ ውስጥ የተፈጸመው ይህ ድርጊት ከ20 አመት በፊት የተከሰተ እንደሆነም ታውቋል።