(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 24/2009)የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት ኢንተርፕራይዝ በመንግስት ትእዛዝ ለሜቴክ የሸጣቸው ሁለት መርከቦች ጅቡቲ ወደብ ላይ ያለስራ ስድስት ወራት መቆማቸው ተገለጸ።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ሐገሪቱ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ያህል ያለኣአግባብ ማውጣቷንና እየተፈጸሙ ባሉ ሕገ-ወጥ ርምጃዎች የሃገሪቱ መልካም ስም እየተጎዳና ገጽታዋ እየተበላሸ መሆኑም ተገልጿል።
በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለነበሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የጻፉት ደብዳቤ እንደሚያስረዳው ሜቴክ መርከቦቹን ቆራርጦ ብረቱን ለመጠቀም በሽያጭ መልክ ተላልፎልታል።
ዘግይቶ እንደታወቀው ግን ሜይቴክ ተፎካካሪ ንግድ መርከብ ለማቋቋም ሲንቀሳቀስ ተግኝቷል።
በህወሃቱ ታጋይ ብርጋዴር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የሚመራው ሜቴክ ‘’አብዮት’’ እና ‘’አባይ’’ የሚባሉትን መርከቦች ከገዛ በኋላ መልህቃቸውን ጥለው ያለስራ በመቆማቸው በየቀኑ ለወደብ ኪራይ ሁለት ሺህ ዶላር ይከፈል እንደነበር ደብዳቤው አመልክቷል።
ደብዳቤው እስከተጻፈበት የካቲት 1/2008 ድረስ የኪራዩ ሂሳብ 391 ሺህ ዶላር ሲደርስ የነዳጅ ወጪና ለሰራተኞቹ አቅርቦትና አገልግሎት ደግሞ አንድ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ እንደተደረገ አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ ለዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የጻፉትና ኢሳት እጅ የገባው ሰነድ ያስረዳል።
እነዚህ መርከቦች ያለስራ በቆሙበት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 1 ሚሊዮን 390 ሺህ ዶላር ከአንድ ድሃ ሃገር ሃብት ላይ ያለበቂ ምክንያት እንዲባክንባቸው ተደርጓል።” በማለት አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ ቁጭታቸውን ገልጸዋል።
የውጭ ሃገራት ዜጎችን ጨምሮ 36 መርከበኞችም ያለስራ ደሞዝ እየተከፈላቸው መሆኑንም ደብዳቤው ያሳያል። የመከላከያና ብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን መርከቦቹን ሲገዛ የተስማማው አካላቸውን አፈራርሶ ብረታብረቶቹን ለመጠቀም እንደሆነ ቢገልጽም ኮርፖሬሽኑ መርከቦቹን ለማስጠገን መንቀሳቀሱን የገለጹት አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ ለንግድ መርከብ ተፎካካሪ ሆኖ መምጣት ለምን አስፈለገ በማለትም ጠይቀዋል። እስከዛሬ የቆሙበትን ወጪስ ማን ይከፍላል ሲሉ አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ ለዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የጻፉት 4 ገጽ ደብዳቤ ያሳያል።
በደብዳቤው ላይ አምባሳደሩ እንደጠቆሙት ሜቴክ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሹ ወታደራዊ ትጥቆችን ጭምር ቴክኒካዊ ብቃታቸው ባልተረጋገጠ የባእዳን መርከብ በማጓጓዝ ከፍተኛ ወጪ እያወጣ ይገኛል።
ጉዳዩን በቁጭት የሚያነሱት አምባሳደር ሱለይማን ይህ ሳያንስ ሌላ ንግድ መርከብ የማቋቋሙ ሃገራዊ ፋይዳ ምንድነው ሲሉም ጠይቀዋል።
መርከቦቹ ከፍተኛ ወጪ ከወጣባቸው በኋላ አንድ ቦታ ቆመው ነዳጅ በመጨረሳቸው ጭራሹኑ አንዱ መርከብ ሞተርና ጄኔሬተሮቹ ጠፍተዋል። በዚህም የተነሳ መርከበኞቹ የባህር ውሃ ለመጠቀም በመገደዳቸው መርከበኞቹ ለተቅማጥ ወረርሽኝ መጋለጣቸውን ነው የገለጹት።
በዚህም ከተጠቁት አንድ ትውልዱ ጋናዊ የመርከቧ ቺፍ ኢንጂነርን ለማሳከምና ውሃ ለማቀበል ሲባል መርከቡ ተገፍቶ መልህቁን መልቀቁን ገልጸዋል።
ጋናዊው ቺፍ ኢንጅነር ሳሙኤል አሙኮ ህክምናውን ካገኘ በኋላ መርከቡ ላይ ተኝቶ መቆየቱን በመቃወም አለም አቀፍ ህግ በማይገዛው ድርጅት ውስጥ አልሰራም በማለት የደረሰበትን በደል ለጅቡቲ ፖሊስ አቤቱታ ማቅረቡን አምባሳደር ሱለይማን ለዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የጻፉት ደብዳቤ ያስረዳል።
የጅቡቲ ፖሊስ ስለጉዳዩ ለአለም አቀፍ የመርከበኞች ማህበር ሪፖርት ካደረገ የኢትዮጵያ መርከቦች በሙሉ ብላክሊስት ውስጥ ይገባሉ በማለት ስጋታቸውን የገለጹት አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱለይማን ደደፎ በየካቲት ወር 2008 በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለነበሩት ቴዎድሮስ አድሃኖም የጻፉትን አራት ገጽ ደብዳቤ ሲያጠቃልሉም የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት መልካም ስምና የሃገራችን ገጽታ ከመበላሸቱ በላይ ሜቴክ ከህገ-ወጥ አድራጎት እንዲቆጠብ መመሪያ እንዲሰጥበት በአክብሮት እጠይቃለሁ ብለዋል።