(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 20/2009)የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር መሆናቸውን ምርጫ ቦርድ ከወራት በፊት ያጸደቀላቸው አቶ የሺዋስ አሰፋ መታሰራቸው ታወቀ።
አቶ የሺዋስ አሰፋ የታሰሩት በባህር ዳር ከተማ ሲሆን የአባላቶቻቸውን የፍርድ ሂደት ለመከታተል በሄዱበት መታሰራቸው ተመልክቷል።
የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አበባ አካሉ ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት አቶ የሸዋስ የታሰሩት ትላንት ረቡእ ሲሆን የታሰሩበት ምክንያት ግን እስካሁን አልታወቀም።
ነሐሴ 1 ቀን 2008 በባህርዳር ከተካሄደው ትእይንተ ህዝብ ጋር በተያያዘ ተጠያቂ ናቸው በሚል ላለፉት 10 ወራት በእስር ቤት የቆዩ የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን የፍርድ ሂደት ለመከታተል የሔዱት አቶ የሺዋስ ጉዳያቸውን ጨርሰው ወደ አዲስ አበባ ሊመለሱ በዝግጅት ላይ እንዳሉ መንገድ ላይ ተይዘው መታሰራቸውን ፓርቲው አስታውቋል።
ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ አቶ የሽዋስ አሰፋ ስለታሰሩበት ምክንያት የታወቀ ነገር የለም።
አቶ የሺዋስ አሰፋ ከዚህ በፊት በአሸባሪነት ተከሰው ከአንድ አመት በላይ በወህኒ ቤት ቆይተው መለቀቃቸው ይታወሳል።