(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 20/2009)ባለፈው ማክሰኞ በቁጥጥር ስር መዋላቸው የተገለጸው 34ቱ ግለሰቦች ዛሬ ሀሙስ ፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል።–የቀረበባቸውም ክስ ተነቦላቸዋል።
ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የቀድሞውን የባለስልጣኑን ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃዱ ሃይሌን ጨምሮ ሶስት ኢንጂነሮች የታሰሩ ሲሆን ሚስተር ሚናሽ ሌቪ የተባሉ የኮንስትራክሽን ድርጅት ባለቤትም አብረው ታስረዋል።
ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ሃላፊነታቸው ያልተገለጸ 7 ሰዎች ታስረው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።ሆኖም ግን የቀድሞው የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዛኢድ ኢብራሂም ሆነ የአሁኑ ስራ አስኪያጅ አቶ አርአያ ግርማይ በክሱ ውስጥ አልተካተቱም።–ሁለቱም የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አባላት መሆናቸው ታውቋል።
ከመተሃራ ስኳር ፋብሪካ በዝቅተኛ የሃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ 4 ሰዎች ታስረዋል።
ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የአገዳ ተከላ ክፍል ምክትል ሃላፊን ጨምሮ 6 ግለሰቦች ታስረው ፍርድ ቤት ቀረበዋል።
ከኦሞ ኩራዝ ሃላፊነታቸው ያልተገለጸ አንዲት እንስትን ጨምሮ አራት ሰዎች ታስረዋል።
ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህግ ባለሙያዎችን ጨምሮ 11 ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ቢሆንም የቀድሞው ሚኒስትር አቶ ሶፊያን አህመድም ሆነ የአሁኑ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም ተከስተ በክሱ ውስጥ አልተካተቱም።
በአጠቃላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት 34 ተከሳሾች በሀገር ሀብት ላይ በድምር የሁለት ቢሊዮን ብር ጉዳት አድርሰዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
የዋስትና ጥያቄያቸው በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ውድቅ ሆኖ ለነሀሴ 3/2009 በተለዋጭ ቀጠሮ እንዲቀርቡ ተወስኗል።
ከፍተኛ የሀገር ሀብት እንደተካሄደበት የተገለጸው ስኳር ኮርፖሬሽንን በሃላፊነት ለረጅም አመታት የመሩት አቶ አባይ ጸሃዬ የበርካታ ቢሊዮን ብሮች ብክነት ተጠያቂ መሆናቸው ሲገለጽ ቆይቷል።
በዚህ ከውጭና ከሀገር ውስጥ ባንኮች በተገኘ ብድር ወደ 70 ቢሊየን ብር ያህል ወጥቶበታል የተባለውን ፕሮጀክት በማዳከምና በመዝረፍ ከአቶ አባይ ጸሃዬ ጋር የሚጠቀሰው ሜቴክ የተባለው በህውሃቱ ታጋይ ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የሚመራው ሜቴክ ቢሆንም እነሱን ግን ተጠያቂ ያደረገ የለም።
ከጋምቤላ እርሻ ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ ወደ 5 ቢሊየን ብር የሀገር ብክነት የተካሄደበትና ይህም በጥናት ይፋ የሆነበት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ብድሩን ወስደው ባባከኑትና በተሰወሩት እንዲሁም በባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረ ላይ የተወሰደ ርምጃ የለም፡፡
አቶ ኢሳያስ ባህረ የ5 ቢሊየኑ ብክነት ከተጋለጠ በሗላ በህዳር 2009 በአቶ ጌታሁን ናና የተተኩ ቢሆንም በሙስና ጉዳይ ግን ተጠያቂ አልሆነም።
አቶ ኢሳያስ ባህረ የህወሃት አባል መሆናቸው ሲታወቅ ብድሩን ወስደው ያባከኑትም በትንሹ ከ98 በመቶ በላይ የህወሃት አባላት መሆናቸውን መረዳት ተችሏል።