ሐምሌ ፲፰ ( አሥራ ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው የችሎቱን ውሎ ተከታትሎ በፌስቡክ ገጹ ላይ እንደዘገበው በእነ መልካሙ ክንፈ የክስ መዝገብ በሽብር ተከሶ ቂሊንጦ እስር ቤት ታስሮ የነበረው ወጣት አየለ በየነ ነገሰ ፣ ህክምና እንዳያገኝ ተከልክሎ ህይወቱ አልፏል። ወጣት አየለ በየነ ህክምና ተከልክሎ ለሞት እንደተዳረገ በአባሪነት የተከሱት እስረኞች፣ ሀምሌ 18/2009 ዓ.ም ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4 ወንጀል ችሎት ገልፀዋል፡፡
ተከሳሾቹ የፀረ ሽብር አዋጁ ከሚፈቅደው አራት ወራት በተጨማሪ፣ 5 ወራት በአጠቃላይ 9 ወራትን ማዕከላዊ ታስረው እንደቆዩ የተገለፀ ሲሆን፣ ሟች ለረዥም ጊዜ ታሞ ህክምና ቢጠይቅም ህክምና ሳይገኝ ቀርቷል ተብሏል፡፡ ህመሙ ከጠናበት በኋላም ከ10 ቀን በላይ ምግብ መብላት ባለመቻሉ ለእስር ቤቱ አስተዳዳሪዎች ጥያቄ አቅርበው መልስ ሳያገኙ መቅረታቸውንና በመጨረሻ ከእስር ቤቱ ውጭ እንዲታከም ቢታዘዝለትም በተቋሙ አፋጣኝ ህክምና ማግኘት ባለመቻሉ ህይወቱ ማለፉን ተከሳሾቹ ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል፡፡
ቀሪዎቹ ተከሳሾችም ህክምና ሊያኙ ባለመቻላቸው ለህይወታቸው እንደሚሰጉ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታቸው አሰምተዋል፡፡ 1ኛ ተከሳሽ መልካሙ ክንፈ ታሞ በየወሩ ህክምና እየወሰደ የነበር ቢሆንም፣ መርማሪዎች የፈለጉትን መረጃ ስላልሰጠ ህክምና መከልከሉንና የሟች እጣፈንታ ሊደርስበት እንደሚችል ስጋቱን ለፍርድ ቤት ገልፆአል፡፡ ‹‹አውቀው ነው የገደሉት፡፡ እኛንም ይገድሉናል፡፡›› ያለው 1ኛ ተከሳሽ ንፁህ በመሆናቸውና መረጃ ስላልተገኘባቸው ህጉ ከሚፈቅደው ውጭ ለ9 ወራት ማዕከላዊ መቆየታቸው ይህም ለንፁህነታቸው ማስረጃ እንደሆነ ገልፆአል፡፡ ማች ንፁህ በመሆኑም ክሱ እንዳይቋረጥ፣ ምስክሮችም ተሰምተው የፍርዱን ሂደት ማወቅ እንደሚፈልጉ ገልጾአል፡፡
4ኛ ተከሳሽ ይማም መሃመድ ‹‹ይህን የሚያደርገው መንግስት ከሆነ ቁርጡን አውቀነው እንሞታለን›› ሲል ተናግሯል፡፡ ‹‹አየለን ሞተ ማለት አልችልም፡፡ ተቀጠፈ ነው የምለው፡፡ የሞተው ዘመድ አጥቶ አይደለም፡፡ ጓደኛና ቤተሰብ አጥቶ አይደለም፡፡ የሞተው ህክምና የሚሰጠው አጥቶ ነው›› በማለት ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።
ቂሊንጦ እስር ቤት ሀምሌ 17/2009 ዓ.ም ተከሳሽ መሞቱን ለፍርድ ቤት ቢገልጽም ፣ በምን ምክንያት እንደሞተ እንዳልገለፀ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ቂሊንጦ ሟች በምን እንደሞተና ለሞቱ ማረጋገጫ ባልላከበት ሁኔታ ግለሰቡ መሞቱን እርግጠኛ መሆን ስለማይቻል እስር ቤቱ ለሀምሌ 26/2009 ዓ.ም ተከሳሹ ስለመሞቱ የሚያሳይ ማረጋገጫና የሞተበትን ምክንያት እንዲያመጣ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
2ኛው ተከሳሽ አየለ በየነ ከኦነግ መሪ ዳውድ ኢብሳ ጋር ግንኙነት በመፍጠር እና ሀገር ውስጥ ያሉ መረጃዎችን ሪፖርት በማድረግ ክስ ቀርቦበት ነበር፡፡ ወንድሙ ቦንሳ በየነም በዚሁ ክስ መዝገብ ስር ክስ ተመስርቶበታል፡፡
አየለ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የወረዳ 10 ስራ አስፈፃሚ አባል ነበር።