(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 17/2009)በስፔን የሚታተመው እለታዊ ጋዜጣ ላቫንጋርዲያ ሐምሌ 16/2009 ባወጣው እትሙ ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ የተጓዘ አንድ ስፔናዊ በዝሆን ተመቶ ህይወቱ ማልፉን አስነብቧል።
ስሙ ያልተጠቀሰው ጎብኚ ጨበራ ጩርጨራ በተባለውና ደቡብ ኢትዮጵያ በሚገኘው የእንስሳት መጠበቂያ ስፍራ ከባለቤቱ ጋር ለጉብኝት የወጡት ከሳምንት በፊት ነበር።
ጎብኚው ለአደጋ የተጋለጠው ከመኪናው ወርዶ በቅርብ ርቀት ዝሆኑን ፎቶ ለማንሳት በሞከረበት ወቅትም እንደሆነ ከዘገባው መረዳት ተችሏል።
ጋዜጣው የአይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው ጎብኚው የህይወት ዋጋ የከፈለው መመሪያ ባለመቀበሉ ወይንም መመሪያዎችን ችላ በማለቱ ነው።
የጎብኝውን መሞት ተከትሎ በቀረበው በዚህ ዘገባ መሰል አደጋዎች በቅርብ ጊዜያት ውስጥ መፈጸማቸውን አስታውቋል።
ባለፈው አመት የካቲት ወር አንድ የብሪታኒያ ጎብኚ በተመሳሳይ ታይላንድ ውስጥ በዝሆን ተገድሏል።በወቅቱም የ16 አመት ልጁ አብሮት እንደነበር ታውቋል።
በዚያው አመት ግንቦት የ24 አመት ወጣት ኢንዶኔዥያ ውስጥ በዝሆን ጥቃት ህይወቱን አጥቷል።