(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 17/2009)በኤሌክትሪክ ሃይል ማጣት ስራ መጀመር ያልቻሉት የአማራ ክልል 197 ፕሮጀክቶች ከ6 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ የወጣባቸው ናቸው።
ፕሮጀክቶቹ ስራ ቢጀምሩ ደግሞ ከ18 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥሩ እንደነበር የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገልጿል።
የኮሚሽኑ የፕሮሞሽንና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይሄነው አለም ለሪፖርተር እንደገለጹት በክልሉ ያለው የሃይል አቅርቦት የክልሉን ልማት ወደ ኋላ እያስቀረው ነው።
ዳይሬክተሩ ይህን ይበሉ እንጂ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ወሳኝ ሚና ያላቸው የኤሌክትሪክ ሃይል ማስፋፊያዎች ተገንብተዋል በሚል በምላሹ አስተባብሏል።
የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዋና ስራ አስፈጻሚዋን ኢንጂነር አዜብን ጨምሮ ከዚህ ቀደም በነበረና በአማራ ክልል በተካሄደ ግምገማ ችግሩን አምነው መቀበላቸው ይታወሳል።
በአማራ ክልል በርካታ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ቢወስዱም በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግር ፣መሬት ባለመዘጋጀቱ፣ በብድር አገልግሎት እጦትና በክትትል ድጋፍ ማነስ ጋር በተያያዘ ተግባራዊ ያልሆኑ በርካታ ናቸው።
በኢንቬስተሮች በኩል መሬት አጥሮ መያዝና አዋጭ እቅድ ያለማምጣት ችግሮችም ተጠቃሽ መሆናቸውን የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታውቋል።
በአማራ ክልል የሚመረተው የኤሌክትሪክ ሃይል በሃገሪቱ ከሚመረተው 43 በመቶ ያህሉን እንደሚሸፍን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህም ሆኖ ግን በኤሌክትሪክ አቅርቦት ማጣት ፋብሪካዎች ሊሰሩም ሆነ ሊገነቡ አልተቻለም መባሉ የክልሉን ህዝብ እያበሳጨ ይገኛል።በሀገሪቱ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል የለም በሚል።