ከቀን ገቢ ግብር ጋር ተያይዞ የተነሳው ህዝባዊ ተቃውሞ ቀጥሏል

(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 17/2009))መርካቶ ዛሬ በአብዛኛው ክፍል አድማ ተመቷል።ከጣና የገበያ አዳራሽ አንስቶ በምናለሽ ተራ፣ሶማሌ ተራ፣ሲዳሞ ተራ፣ጎጃም በረንዳ ምእራብ ሆቴል አካባቢ ዛሬ አድማውን ተቀላቅለዋል።

የጣና ገበያ አዳራሽ ሱቆች ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል።ከግብር መስሪያ ቤት የደረሳቸው ተመን ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ስራቸውን ለማቆም እንደተገደዱ ዘጋቢያችን ያነጋገራችው ነጋዴዎች ገልጸዋል።

ዘግይተው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአንዳንድ አድማ በመቱ የመርካቶ ስፍራዎች የመንግስት ደህንነቶችና ታጣቂዎች እየተዘዋወሩ በማስፈራራት ላይ ናቸው።

በዱባይ ተራና ራጉኤል አካባቢዎች ሱቃቸውን እንዲከፍቱ በታጣቂዎች የሃይል እርምጃ እየተወሰደባቸው ቢሆንም ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ መደብሩን የከፈተ የለም።

እስከ ምሽት ድረስ ከመሃል መርካቶ ምናለሽ ተራ እስከአንዋር መስጊድ ያሉ ሱቆች፣መደብሮችና ጉልቶች ሙሉ በሙሉ ስራ አቁመዋል።

ለወትሮው በሰው ትርምስ የሚታወቀው መርካቶ ጭር ብሎ ውሏል።ዘግይቶ በደረሰን መረጃ ከመርካቶ ሌላ ሩፋኤልና ሸጎሌ አካባቢዎች አድማ እንደተመታባቸው ለማወቅ ተችሏል።በቄራ አካባቢ የሚገኙ አንዳንድ ሱቆችና መደብሮች ተዘግተው መዋላቸው ታውቋል።

መርካቶ ዛሬ የተወሰደው አድማ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን ባለፈው ሳምንት በኮልፌ፣አጣና ተራ፣ብሔረ ጸጌ አካባቢዎች ተነስቶ የነበረው አድማ ዳግም ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

በአማራ ክልል በተለይም በጎጃም የስራ ማቆም አድማ የተወጣባቸው ከተሞች ቁጥር እየጨመረ ነው።ባለፈው ሳምንት ከሐሙስ ጀምሮ አድማ የመታው ሸብል በረንታ ዛሬም ቀጥሏል።

አንድ ነጋዴ መታሰራቸው ደግሞ ይበልጥ የህዝቡን ተቃውሞ አጠናክሮታል።ነጋዴው ካልተፈቱ ሌላም እርምጃ እንወስዳለን ብለዋል ነዋሪዎቹ።

አድማው በብቸናና ሞጣም የተጀመረ ሲሆን ሱቆችና መደብሮች ተዘግተው እንደዋሉ በፎቶግራፍ ተደግፎ የወጣው መረጃ አመልክቷል። በደጀንም እንዲሁ አድማው በነጋዴዎች መመታቱ ታውቋል።ከቤንዚን መጥፋትና ከተሽከርካሪዎች የፍቃድ ግብር መጨመር ጋር በተያያዘ በደብረታቦር የተቃውሞ ጥሪ እየተደረገ ነው።በባህርዳርና በደብረማርቆስም እንዲሁ ወረቀት ተበትኗል።በሸዋሮቢት ሰሞኑን አጠቃላይ የስርአት ለውጥ የሚጠይቅ ወረቀት ሲበተን እንደነበር ያገኘንው መረጃ አመልክቷል።

መንግስት በጉዳዩ ላይ ግልጽ መረጃ መስጠት አልቻለም።አቶ ከበደ ጫኔ የጉምሩክ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በመንግስት ደጋፊ ጋዜጦች ላይ የግብር ተመኑ ቀርቷል ማለታቸው ተዘግቧል።በማግስቱ በሌላ የፓርቲ ሚዲያ ላይ ቀርበው የተናገሩትን ሀሰት ነው በማለት አስተባብለዋል።በሌላ በኩል በኦሮሚያ እስከ ነሐሴ 15 የክፍያ ጊዜው መራዘሙ ተጠቅሷል። ይሁንና መንግስት ስለዚህ ውሳኔ በይፋ የገለጸው ነገር የለም። በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በዋናነትም በኦሮምያና በአማራ አድማው ተጠናክሮ የቀጠል ሲሆን በደቡብ ክልልም አንዳንድ ቦታዎች እንቅስቃሴው እየተካሄደ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።