(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 14/2009)የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ ባሳለፍንው ሳምንት የአዲስ አበባ ማእከላትና ኮሪደሮች ልማት ኮርፖሬሽን እንደሚቋቋምና ኮርፖሬሽኑ ስራ እንደሚጀምር ገልጸው ነበር።
በዚሁም መሰረት ከአፍሪካ ህብረት እስከ ቤተ መንግስት ከሚገኙ ቦታዎች 300 ሔክታር መሬት በማስለቀቅና በማዘጋጀት ስራውን እንደሚጀምርም ገልጸዋል።
ይህንን ተከትሎም የአካባቢው ነባር ነዋሪዎች ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ወደ ቂርቆስ ክፍለ ከተማና በስሩ ወዳሉ ወረዳዎች ለቤት እድሳትና ከመሬት ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን ለማግኘት የሄዱ የአካባቢው ነዋሪዎችን ያነጋገሩት የኢሳት ምንጮች ነዋሪዎቹ እየደረሰባቸው ያለው ከፍተኛ መጉላላት ምሬት እንደፈጠረባቸው መረዳት ችለዋል።
የወረዳው መሬት አስተዳደር ሰራተኞችና ሙያተኞች ለነዋሪዎቹ እንደገለጹት የአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ አዲሱ ኮርፖሬሽን በሙሉ አቅሙ ስራ እስኪጀምር ድረስ ከእድሳትና መሰል አገልግሎቶች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች እንዲዘገዩ የቃል መመሪያ ተላልፏል።
ከነባር ቦታዎች የሚነሱ ነዋሪዎች ተለይተው እስኪታወቁ ድረስ እድሳትና ተያያዥ አገልግሎቶችን መፍቀዱ ለተፈናቃዮች የሚከፈለውን ካሳ ስለሚያሳድገውና ሌሎች ጥያቄዎችን ሊያስነሳ ስለሚችል ቢሮክራሲያዊ በሆነ መንገድ አገልግሎቱን ማራዘም እንዳለባቸው የወረዳው መሬት አስተዳደር ሙያተኞች ለኢሳት ምንጮች አስታውቀዋል።
አዲስ የተቋቋመው ኮርፖሬሽን መሬት ከነባር ነዋሪዎችና ድርጅቶች የማስለቀቅ፣ለተፈናቀሉት ካሳ የማዘጋጀትና የመክፈል፣የሚተላለፉ መሬቶችን ከማንኛውም ይገባኛል ጥያቄዎች ነጻ አድርጎ የማስተላልፍና የማስተዳደር ስልጣን እንደተሰጠው በአዋጁ ላይ እንዲካተት ተደርጓል።