ሐምሌ ፲፬ ( አሥራ አራት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ፣ ከአልሸባብ ጋር በተደረጉ ውጊያዎች ሁሉ የተሳተፉና በተለያዩ ምክንያቶች መከላከያን የለቀቁ የቀድሞ ምልስ ወታደሮች አቤቱታቸውን ማሰማታቸውን ቀጥለዋል። በደሴ የሚገኙ የተመላሽ ሰራዊት አባላት፣ አገዛዙን ደማችን አፍስሰን አጥንታችን ከስክሰን ብናገለግለውም፣ ባለስልጣኖቻችን እንደ ቆሻሻ እያዩ፣ የትም ጥለውናል ብለዋል። መከላከያን መቀላቀል የሚፈልጉ ወጣቶች እነሱን አይተው ትምህርት እንዲወስዱም ይመክራሉ።
“ እኛ ወደ ህዝቡ ስንመለስ፣ ህዝቡ እኛን ለመቀበል አይፈልግም፣ በረጅም ጊዜ ሂደት ህዝቡ ሲቀበለን፣ አመራሩ አይቀበልንም” የሚሉት ወታደሮች፣ አገዛዙ ምንም እንዳላደረገላቸውና የመከራ ኑሮ እንደሚኖሩ ይገልጻሉ።
“እንደ ቆሻሻ ነው የምንታየው” የሚሉት ወታደሮች፣ እነሱም ቤተሰቦቻቸውም ኑሮአቸውን ለመግፋት ተችግረዋል።
በወታደሮች መካከል ያለው የብሄር ልዩነት በመከላከያ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የኑሮ ልዩነት እየፈጠረ ነው። የህወሃት አባል የሆኑ ወታደሮች የተለያዩ ማእረጎችን በቀላሉ በማግኘት፣ ከፍተኛ ገንዘብ በመሰብሰብ፣ መከላከያን ሲለቁ ችግር ላይ እንደማይወድቁ፣ የሌሎች ብሄር አባላት ወታደሮች ግን በመካለከያ ውስጥም ሆነ መከላከያን ከለቀቁ በሁዋላ፣ በስቃይ እንደሚኖሩ ተመላሽ ወታደሮች ይገልጻሉ። የወጡበት ማህበረሰብም አገዛዙን ስለሚጠላ እነሱንም በዛው መነጽር እያየ እንደሚያገላቸውና እንደማይቀበላቸው ወታደሮቹ ይገልጻሉ።
ወጣቶች ወደ መከላከያ ከመግባታቸው በፊት ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል የሚሉት ተመላሽ ወታደሮች፣ አሁን በአግልግሎት ያሉት ወታደሮችም፣ ሲወጡ የሚጠብቃቸው ስቃይና መከራ በመሆኑ፣ ከአሁኑ መብታቸውን ሊያስከብሩ ይገባል ሲሉ ፣ የሚገጥማቸውን ከባድ ህይወት በመተረክ ምክራቸውን ይለግሳሉ።
በመከላከያ ውስጥ የትግራይ ተወላጆች አብዛኛውን የአዛዥነት ቦታዎች ለመያዝ የቻሉት የአማራ ተወላጆች መካለከያን ለመቀላቀል ፍላጎት ስለሌላቸው ክፍተት በመፈጠሩ ነው በማለት አንድ የብአዴን ባለስልጣን መናገራቸውን ኢሳት ድምጻቸውን ቀርጾ ማቅረቡ ይታወቃል።