ሐምሌ ፲፪ ( አሥራ ሁለት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ፣አቃቤ ህግ በእነ ንግስት ይርጋ ላይ ሊያቀርባቸው የነበሩት ምስክሮች እንዲታለፉ ብይን ሰጥቷል። አቃቤ ህግ 7 ምስክሮችን አቀርባለሁ ብሎ አስመዝግቦ የነበረ ሲሆን 2ቱን እንደማይፈልጋቸው በመግለጽ አሰናብቷቸዋል። ሶስቱን ምስክሮች ለማሰማት ፍርድ ቤቱ አራት ጊዜ ለፖሊስ ቀጠሮ ቢሰጥም፣ ፖሊስ ምስክሮችን ላገኛቸው አልቻልኩም በማለቱ ለ5ኛ ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር። ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ቀጠሮ ይሰጥ፣ አይሰጥ በሚለው ላይ ለመወሰን ዛሬ ረቡዕ ከቀጠረ በሁዋላ፣ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ አሳማኝ ምክንያት ሊያቀርብ አልቻለም በማለት፣ አቃቢ ህግ አቀርባቸዋለሁ ያላቸው ምስክሮች እንዲታለፉ ወስኗል።
በሌላ በኩል አንደኛ ተከሳሽ ንግስት ይርጋ በሴትነቷ የደረሰባትን ከፍተኛ ጥቃት በማስታወስ ያቀረበችው አቤቱታ ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲደርስና መስሪያ ቤቱ ምላሽ እንዲሰጥበት ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቶአል።
ፍርድ ቤቱ ብይን ለመስጠት ለነሃሴ 12 ቀጠሮ ሰጥቶአል። እንዲሁም ወጣት ንግስት ባቀረበችው አቤቱታ ላይ የቃሊቲን ምላሽ ለመስማት ለሃምሌ 20 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶአል።
በእነ ወጣት ንግስት ላይ እስካሁን የተሰሙት ምስክሮች ሁለት ብቻ ናቸው።