(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 11/2009) የኤፈርት ንብረት የሆነውና በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማራው ትራንስ ኢትዮጵያ በ372 ሚሊየን ብር ያስገነባው ዋና መስሪያ ቤትና የጎማ አገልግሎት መስጫ ማእክል ተጠናቆ ስራ ጀምሯል።
በ3 ሚሊየን ብር ካፒታል ክ650 የጭነት መኪናዎች በላይ በመያዝ የትራንስፖርት ዘርፉን በበላይነት የሚመራውና የህወሃት ንብረት እንደሆነ የሚታወቀው ትራንስ ኢትዮጵያ በ372 ሚሊየን ብር በአዲስ አበባ ያሰራውን ህንጻ አስመርቋል።
ህንጻውን መርቀው የከፈቱት የኤፈርት ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አዜብ መስፍን ናቸው።
ትራንስ ወርቅ ኩባንያቸው መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ አዜብ ኩባንያው በፈጣን እድገትና ከፍተኛ ትርፋማነት ላይ ደርሷል ነው ያሉት በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ።
ትራንስ ኢትዮጵያ አሁን በያዘው ስራ ብቻ የሚቆም ሳይሆን ተጨማሪ ስራዎችን ለመስራት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ወይዘሮ አዜብ ተናግረዋል።
የህወሃት ንብረት የሆነው ትራንስ ኢትዮጵያ ከዋና መስሪያ ቤቱ ዘመናዊ ህንጻ ጎን ለጎን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ያስገነባውን የጎማ አገልግሎት መስጫ ማእከል በተመሳሳይ ቀን አስመርቋል።
የአገልግሎት መስጫ ማእከሉ ፒሬሌ ከተሰኘው አለም አቀፍ የተሽከረካሪ ጎማ አምራች ኩባንያ ጋር በመሆን በጥምረት ያስገነባው መሆኑን በምርቃቱ ስነ ስርአት ላይ የትራንስ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተፈሪ ዘውዱ ገልጸዋል።
ትራንስ ኢትዮጵያ የእርዳታ እህሎችንና ማዳበሪያ ከጅቡቲ ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሞኖፖሊ ሲያመላልስ እንደነበር ይታወቃል።
በአሁን ሰአት አገልግሎቱን በማስፋትም ለስካኒያ ምርት የኢትዮጵያና የጅቡቲ ወኪል በመሆን የስካኒያ አውቶቡስ፣የጭነት ተሽከርካሪዎችንና ሞተሮችን በማስመጣት በማከፋፈል ላይ ይገኛል።
በኢህአዲግ ዘመነ መንግስት የወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎች ህግ ፓርቲዎች በንግድ ስራ ላይ መሰማራት እንደማይችሉ መደንገጉ ይታወሳል።
ህጉ ይደንገግ እንጂ በህወሃት ባለስልጣናት የቦርድ አባልነትና ስራ አስፈጻሚ የሚመራው ኤፈርት ከፍተኛ ትርፍ በሚያስገኙና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በተቆጣጠሩ ዘርፎች ላይ መሰማራቱ የሚታይ ሃቅ ነው።
ይህ ደግሞ በተደጋጋሚ ከፍተኛ ገቢ አላቸው በሚባሉ ነጋዴዎች ዘንድ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያስንሳ እንደነበር የሚታወስ ነው።