(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 11/2009)የኢትዮጵያ የስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በኢንተር ኮንቲነንታል ሆቴል ባለቤት አቶ ስማቸው ከበደ ላይ ክስ የመሰረተው እንደ ኣአውሮፓዊያን ኣአቆጣጠር በግንቦት 2013 ነበር።
በዋናነት ክሱን ሲመሰርትም አቶ ስማቸው ከታክስ ማጭበርበርና ከሙስና ጋር በተያያዘ የሰሩት ወንጀል አለ በሚል ነው።
ግለሰቡ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ከፍተኛ አመራር ከነበሩት ከአቶ መላኩ ፈንታና ከአቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ ጋር በመተባበር የሰሩት ወንጀል ግንኙነት አለው የሚለውም ኮሚሽኑ አያይዞ ያቀረበው ክስ ነበር።
አቶ ስማቸው ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ የግንባታ ማጠናቀቂያ እቃዎችን አላግባብ ጥቅም ላይ አውለዋል፣ በህገወጥ መንገድም ለሶስተኛ ወገን ሲያስተላልፉ ተገኝተዋል ሲል አቃቢ ህጉ ክሱን አጠናክሯል።
በአውሮፓውያኑ 2015 አቶ ስማቸው ከገቢዎች ባለስልጣናት ጋር በተያያዘ የተከሰሱበት ወንጀል ይነሳልኝ በሚል ያቀረቡት አቤቱታ በፍርድ ቤቱ ተቀባይነት አግኝቷል።
ይህም የሆነው ፓርላማው ከቀረጥ ነጻ የገቡ እቃዎች ወደ ሌላ ማስተላለፍ መታየት ያለበት በወንጀለኛ ህግ ሳይሆን በአስተዳደራዊ እርምጃ ነው በሚል ወሳኔ በማሳለፉ ነው።
በዚህም ምክንያት የኮሚሽኑ አቃቢ ህጎች ክሳቸውን በመቀየር አቶ ስማቸው በ20 ሚሊየን የገቢ ታክስና በ29.4 ሚሊየን ብር ተጨማሪ እሴት ታክስ ተጠያቂ ናቸው የሚል አቤቱታ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል።።
የኮሚሽኑ አቃቢ ህጎች ያቀረቡትን የክስ ፋይል የተመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም አቶ ስማቸውን በ674 ሺ ብር ተጨማሪ እሴት ታክስ ጥፋተኛ ናቸው ሲል በስድስት አመት እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል። አቃቢ ህጉ ሊጠየቁበት ይገባል ብሎ ያቀረባቸውን ተጨማሪ የገንዘብ ማጭበርበር ወንጀሎችን ወደ ጎን በማለት።
ፍርድ ቤቱ በአውሮፓያኑ ሰኔ 14 2017 ባዋለው ችሎት የአቶ ስማቸው ጠበቆች ባለጉዳያችን 4 አመታትን በእስር አሳልፈዋል ስለዚህ በአመክሮ ሊለቀቁ ይገባል በሚል ባደረጉት ርብርብ ከፍርድ ቤቱ የይሁንታ መልስ ማግኘት ችለዋል።
ፍርድ ቤቱ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ይለቀቁ ሲል ለእስር ቤቱ አስተዳደር ደብዳቤ ቢጽፍም አስተዳደሩ ግን በአቃቤ ህግ የቀረበባቸው ቀሪ ይግባኝ አለ በሚል ግለሰቡ ለአንድ ወር ያህል በእስር ቤት እንዲቆዩ አድርጓል።
ከእነ ኣቶ መላኩ ፋንታ ጋር በታክስ ማጭበርበር እና በሙስና ወንጀል ተከሰው የነበሩት አቶ ስማቸው ከበደ ታዲያ በመጨረሻ ከአንድ ወር ውዝግብ በኋላ ከእስር ተፈተዋል።