(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 11/2009) መለዮ ለባሾቹ የሜቴክ አመራሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከስርአቱ ደጋፊዎችና አገልጋዮች እንዲሁም ከፓርላማ አባላት ሳይቀር መብጠልጠል ጀምረዋል።
ይህ ደግሞ ሜይቴክን በተመለከተ በአገዛዙ ውስጥ ሁለት ጎራ እንዳለ አመላካች እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ።
በህወሃቱ ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የሚመራው ሜይቴክ ለሃገር እየተሰዋን ነው ማለቱን የሚደገፍ በአንድ ጎራ፤ የሃገር ሃብት እየባከነና እየተዘረፈ ነው የሚሉት ደግሞ በሌላ ጎራ ተከፋፍለዋል።
ለስርአቱ ቅርበት እንዳለው የሚነገረው የፎርቹን ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ታምራት ገብረጊዮርጊስ በርእስ አንቀጹ ይፋ እንዳደረገውም በወታደሮች የሚመራው ሜይቴክ በአሰራሩ ድክመትና ዝርክርክነት ብሄራዊ ሃፍረትና ውርደት እየሆነ መጥቷል ሲል አስፍሯል።
እናም ሜይቴክ በከፍተኛ የገንዘብ ብክነት፣ ስራን በማጓተትና የንግድ ህግን ተከትሎ ባለመስራት ለውድቀት መዳረጉን በጽሁፉ አመልክቷል።
እንደ ፎርቹን ማኔጂንግ ኤዲተር ታምራት ገ/ጊዎርጊስ ገለጻ ሜይቴክ ግልጽነት የጎደለው ተቋም ብቻ ሳይሆን በሃገሪቱ የጨረታና እና የግዥ ስርአት የማይመራ ቦጥቧጭ ድርጅት ነው።
በዚሁ ዝርክርክ አሰራሩም አቅመቢስና አጥፊ ሲል በአደባባይ የሜቴክን ሃጢያት ዘርዝሯል።
ሜይቴክ በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የኢንደስትሪ አብዮት ያካሂዳል ተብሎ ቢቋቋምም ከዚህ ይልቅ ወደ ዘራፊ ድርጅትነት መቀየሩን ፎርቹው በርእስ አንቀጹ አስነብቧል።
እንደ ጋዜጣው ገለጻ ሜቴክ ከራሱ ውድቀት አልፎ የግል ንግድ ድርጅቶችን ህልውናም እየተፈታተነ ይገኛል።
አንድም ጥራት የጎደላቸው ምርቶቹን ለመንግስት በከፍተኛ ዋጋ እንዲያቀርብ በማድረግ የገበያ ከለላ ተደርጎለታል ነው ያለው። ይህም ገበያን በማዛባትና የሃገሪቱን የንግድ ሚዛን ጉድለት በማባባስ የግሉን ዘርፍ እየገደለ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብሏል።
መንግስት በሜቴክ ጉዳይ ላይ አፋጣኝ የማሻሻያ ርምጃ ካልወሰደ የወታደራዊ ተቋሙ እጣ ፋንታ ዘረፋና ተወዳዳሪ የሌለው አባካኝ ሆኖ እንደሚቀርም ፎርቹን በርእሰ አንቀጹ አመልክቷል።