ሐምሌ ፲፩ ( አሥራ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በተለያዩ ከተሞች ከእለታዊ ገቢ ግብር ጋር በተያያዘ የተጀመረው የነጋዴዎች አድማ ለሁለተኛ ቀን ተጠናክሮ ቀጥሎአል። በአምቦ የንግድ ድርጅቶችና ሌሎች አገልግልሎት ሰጪ ተቋማት እንደተዘጉ ናቸው። በአምቦ መስመር ወደ አዲስ አበባ እና ወደ ወለጋ የሚሄዱ መንገዶች በመዘጋታቸው የተሸከርካሪ አግልግሎት ተቋርጧል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፌደራል ፖሊስ አባላት ከተማዋን ወረው እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ላይ ናቸው።
በጊንጪም እንዲሁ የተቃውሞውን ጥሪ ባለማክበር ሲሰራ የተገኘ አንድ ሚኒባስ ተሽከርካሬ በድንጋይ ተሰባብሯል።
በወሊሶም እንዲሁ አድማው ተጠናክሮ ቀጥሎአል። ሆቴሎችና ሱቆች ተዘጋግተዋል። የባጃጅ አገልግሎት ተቋርጧል። ፖሊሶች ከተማዋን ተቆጣጥረው ቅኝት እያደረጉ ነው። የክልሉ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በአምቦ የተጀመረው አድማ በሰላም መጠናቀቁን ቢናገሩም፣ አድማው ግን ዛሬም ድረስ ለሁለተኛ ጊዜ እንደቀጠለ ነው። አድማው በበርካታ አነስተኛ ከተሞችም በመካሄድ ላይ ነው። በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች አድማውን እንዲቀላቀሉ ጥሪ የሚያደርጉ ወረቀቶች እየተበተኑ ነው።
በደቡብ ኦሞ ዞን ዋና ከተማ ፣ ጂንካና በአካባቢው የሚገኙ ጋዘር፣ ቶልታ እና የመሳሰሉት ከተሞችም መንግስት የህዝቡን ገቢ፣ የኑሮ ሁኔታ ፣ እንዲሁም በየጊዜው ከህዝቡ በልማት ሥም በፈቃድና ጫና /ተጽዕኖ የሚሰበሰበውን ገቢና በባለሥልጣናት የሚመዘበረውን የህዝብ ሃብት ባላገናዘበ መንገድ የከመሩትን የቀን ገቢ ግምት ህዝቡ የማይቀበለው መሆኑ በግልጽ እየተነገረ ነው ፡፡ የንግዱ ማኅበረሰብ ዞናችን በድርቅ በተመታበትና የአርብቶአደር ህዝባችን የኑሮ መሰረት በተናጋበት ወቅት ‹አደጋውን በጋራ ለመመመከት በጋራ ምን ማድረግ እንችላለን› በሚል ሳያነጋግር፣ ዛሬ ‹‹ግብር ለመሰብሰብ መምጣቱን እንቃወማለን› እያሉ ነው።