የያንግ ሩት እንግሊሽ እስኩል ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት ጠፋ

ሐምሌ ፲፩ ( አሥራ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመዲናችን አዲስ አበባ የሚገኘው የያንግ ሩት እንግሊሽ እስኩል ትምህርት ቤት ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ውጤት ጠፍትዋል። ተማሪዎቹ እና ወላጆች በውጤቱ መጥፋት ምክንያት ከፍተኛ ጭንቀት ላይ መውደቃቸውን የትምህርት ቤቱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ታፈሰ ዋቺሶ ለሸገር ኤፍኤም ሬዲዮ ተናግረዋል።
የትምህርት ቤቱ አስተዳደር የፈተናውን ውጤት ለማግኘት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በመመላለስ ደጅ ቢጠኑም ምንም ዓይነት አጥጋቢ ምላሽ ማግኝት አልቻሉም። የትምህርት ቢሮው ባለስልጣናት ለፈተናው መጥፋት ”ውጤቱ ተቀላቅሎ ወደ ሌላ ትምህርት ቤት ሳይሔድ አይቀርም” የሚል አሳማኝ ያልሆነ ምላሽ ተሰጧቸዋል። በተጨማሪም አሉ አቶ ታፈሰ ”የፈተናው ውጤት ቢጠፋም ተማሪዎቹ በሚቀጥለው ዓመት የትምህርት ዘመን ወደ 9ኛ ክፍል ተዘዋውረው መማር ይችላሉ።” የሚል ሕግን ያልተከተለ አሳማኝ ያልሆነ ግብረመልስ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
የተማሪዎቹ ወላጆች የልጆቻችንን ውጤት ስጡን እያሉ ያስጨንቁና ለተማሪዎቹ ሥነ-ልቦና ሲባልም ትምህርት ቢሮው አስቸኳይ የሆነ መላ እንዲፈልግላቸውም ተማጽኖዋቸውን አሰምተዋል። ከያንግ ሩት እንግሊሽ እስኩል በተጨማሪ የሌሎች ሁለት ትምህርት ቤቶች የ8ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሳይጠፋ እንዳልቀረ ከክፍለ ከተማው መስማታቸውንም ምክትል አስተዳደሩ አክለው አስታውቀዋል። ከቅርብ ግዜያት ወዲህ በመላው ኢትዮጵያ የፈተና ውጤቶች መጥፋት የተለመደ ክስተት እየሆነ ነው።