(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 10/2009) ከግብር ጫናና ትመና ጋር ተያይዞ እንደገና ያገረሸው ተቃውሞ በርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎችን እያዳረሰ ይገኛል።
በሕወሃት የሚመራው አገዛዝ በተለያዩ ተሽከርካሪዎች ወደ ኦሮሚያ ተጨማሪ ወታደሮችን እየላከ መሆኑ ተነግሯል።
በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው አምጽ በአምቦ ጀምሮ ጊንጪና ጀልዱ እንዲሁም ወሊሶና ቡራዩን አዳርሷል።
በሻሸምኔ፣በኮፈሌና አርሲም ተመሳሳይ ሕዝባዊ ተቃዋሚዎች መኖራቸው ነው የተነገረው።
በጊንጪ የስራ ማቆም አድማ ሙሉ በሙሉ እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።የንግድ ቤቶች፣ሱቆችና ሆቴሎች ተዘግተዋል።
በአምቦ ሁለት ወጣቶች በጥይት መቁሰላቸውም ተነግሯል።
በኦሮሚያ በስፋት እየተከሰተ ያለው ሕዝባዊ ቁጣና ተቃውሞ ወደ ሌሎች የሐገሪቱ አካባቢዎችም ተዛምቷል።
በደቡብ ክልል ሳውላ ከተማ ከግብር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቷል።–በዚሁ አካባቢ በፍርድ ቤት ትእዛዝ አንድ የወረዳው ካቢኔ አባል በመታሰሩ ይህንኑ የፈጸመው ኢኒስፔክተር ዘላለም የተባለ ፖሊስ አዛዥ በደኢህዴን ስራ አስፈጻሚ አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ ትእዛዝ ከስራና ከሃላፊነት መነሳቱ ታውቋል።
አቶ ተስፋዬ የፖሊስ አዛዡን እንዲታገድ ያደረጉት እንዴት የካቢኔ አባል በፍርድ ቤት ትእዛዝም ቢሆን ታስራልህ በሚል ነው።
በግብር የተማረረውን የሳውላ ህዝብ ያስጨነቁት የወረዳው የካቢኔ አባል የወረዳው የገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ሆነው በሙስና የሚታወቁ መሆናቸውን የኢሳት መነጮች ገልጸዋል።
በአማራ ክልልም ከግብር ጫና ጋር በተያያዘ የባህርዳር ነጋዴዎች ፈቃዳቸውን እየመለሱ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።