(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 10/2009)የአዲስ አበባ መስተዳድር ምክር ቤት ሰሞኑን ጉባኤውን አካሂዷል’።የከተማዋ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የ2008 በጀት ዓመት ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ አቅርቧል።
ሪፖርቱ እንዳመለከተውም ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ያለ አግባብ ባክኗል።– 500 ሚሊየን የሚሆን የህዝብና የመንግስት ገንዘብ ደግሞ በወቅቱ መሰብሰብ አልተቻልም።
ከዚህም ሌላ በወቅቱ ያልተወራረደ 200 ሚሊዮን ብር፣ ለማን እንደተከፈለ ማስረጃ የሌለው 257 ሚሊዮን ብር እንዲሁም አዋጅና መመሪያን ሳይከተል ለውሎ አበልና ለደመወዝ የተከፈለ ከ353 ሚሊዮን ብር በላይ በኦዲት መገኘቱን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ለበጀቱ መባከን የመንግሥት የግዥ መመሪያን ተከትሎ አለመስራት፣ በመመሪያና በህግ ከተፈቀደው በላይ የውሎ አበል ክፍያን መፈፀም የሚሉት በምክንያትነት ተቀምጠዋል፡፡
ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የከተማ አስተዳደሩ ዋና ኦዲተር ወይዘሮ ፅጌወይን ካሣ፤ ብክነትና ምዝበራ በፈፀሙ አካላት ላይ ከፀረ ሙስና እና ከፖሊስ ጋር በመተባበር እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ዶክተር ታቦር ገ/መድህን በበኩላቸው፤ የኦዲት ግኝት ያለባቸው ተቋማት ተለይተው የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድ ለም/ቤቱ አባላት ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ መሥሪያ ቤቶች ያለው የግዥ መመሪያን ተከትሎ ያለመስራት ችግርና ሙስና መፍትሄ ያልተገኘላቸው ችግሮች መሆናቸው በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱ ይታዋሳል።ዘገባውን ያገኘንው ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ነው።