ሐምሌ ፲ ( አሥር ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የእለታዊ ገቢን ተንተርሶ የተጣለውን ግብር በመቃወም ለ3 ቀናት የተጠራው የስራ ማቆም አድማ ዛሬ ሰኞ ተጀምሯል። ባለፈው ሳምንት ተቃውሞአቸውን ወደ አደባባይ በመውጣት ያሰሙት የአምቦ ነዋሪዎች፣ ዛሬ የንግድ ድርጅቶቻቸውንና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመዝጋት ተቃውሞአቸውን በመግልጽ ላይ ናቸው። በአምቦ የመንግስት መስሪያቤቶች፣ ትምህርት ቤቶችና አንዳንድ ባንኮች ተዘግተዋል። ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚወስዱ መንገዶችም ተዘግተዋል።
የስራ ማቆም አድማው በግንጪና ወሊሶም ተግባራዊ እየሆነ ነው። በጊንጪ ህዝቡ ግብር አንከፍልም፣ የታሰሩ መሪዎቻችን ይፈቱ የሚሉና ሌሎችም የለውጥ ጥያቄዎች አቅርበዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፌደራል ፖሊስ ወደ ከተማዋ መግባቱም ታውቋል።
በወሊሶም ተመሳሳይ ተቃውሞ የተነሳ ሲሆን፣ መኪኖች በድንጋይ ተመተዋል። የትራንስፖርት አገልግሎትም ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል፡፡
ተመሳሳይ ተቃውሞ በጉደር ፣ በአርሲ እና በሙገርም መካሄዱ ታውቋል። በአርሲ ወደ ባሌ እና አዋሳ መውጫዎች ባለፉት ሁለት ቀናት ምሽት ላይ መንገዶች ተዘግተው ነበር።
በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ ነጋዴዎች አድማውን በመቀላቀል ተቃውሞአቸውን እንዲያሰሙ የአድማ ጥሪ ወረቀቶች እየተበተኑ መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።