(ኢሳት ዜና- ሀምሌ 7/2009) የኢትዮጵያ ሚዲያ ካውንስል ከዋቢ የግል አሳታሚዎች ማህበር ጋር በመተባበር ለአቶ ክፍሌ ወዳጆ እና ለአቶ አማረ አረጋዊ የሕይወት ዘመን እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
ኣቶ ክፍሌ ወዳጆ ሕገመንግስቱ ሲረቀቅ የሚዲያ ነጻነት በሀገሪቱ እንዲከበር ሚና ተጫውተዋል በሚል ከአቶ አማረ ጋር እውቅና ተስጥቷቸዋል።
በእውቅና አሰጣጡ ላይ የተገኙት ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተአማኒና ተፅዕኖ ፈጣሪ መገናኛ ብዙሃንን ለመገንባት ሁሉም አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
አቶ አማረ አረጋዊ የአፍሪካ ቀንድ ፕሬስ ተቋምንና በቅርቡ ስራ የሚጀምረውን የአፍሪካ ህዳሴ ቴሌቪዥንን እንደሚመሩም ተገልጿል፡፡
አቶ አማረ አረጋዊ እወቅናውን የሰጣቸው ተቋም እራሳቸው የሚመሩት የኢትዮጵያ ሚዲያ ካወንስል መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ግርምታን ፈጥሯል።
በኢትዮጵያ ነጻው ፕሬስ ከተጀመረበት ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር በአሁኑ ጊዜ የሀገሪቱ ሚዲያ እያሽቆለቆለ መሆኑ እየታወቀ አቶ አማረ ለዘርፉ እድገት አስተዋጽኦ አድርገዋል መባሉም አነጋጋሪ ሆኗል።
በአቶ አማረ አረጋዊ የሚመራውን ሪፖርተርን ጨምሮ ከ 3 ያልበለጡ የግል ፕሬስ ውጤቶች ብቻ እንዳሉ ይታወቃል። እነዚሁም አዲስ አድማስ ሰንድቅና ሪፖርተር ናቸው።
የእውቅና ፕሮግራሙ ትናንት ሀሙስ ሀምሌ 6 ቀን 2009 በሂልተን ሆቴል መካሄዱ ታውቋል።
በትናንትናው እለት ኣቶ አማረ አረጋዊ የህይወት ዘመን እውቅና ሊሸልሙ ነው በሚል ባቀረብነው ዜና እሳቸውን የማይወክል የተሳሳት ምስል በመጠቀማችን ይቅርታ እንጠይቃልን ።