በደቡብ ሱዳን ግጭት አገርሽቶ በሺ  የሚቆጠሩ ወደ ኢትዮጵያ ፈለሱ

 

(ሐምሌ- 5/2009)በደቡብ ሱዳን በላይኛው ናይል ፓርክ ግዛት በደቡብ ሱዳን መንግስት ኃይሎችና በተቀናቃኙ የቀድሞው ምክትል ፕሬዝደንት ሪክ ማቸር ወታደሮች መካከል ግጭት በማገርሸቱ በሺ የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን ወደ ኢትዮጵያ ፈልሰዋል።

ሬዲዮ ታማዙጅ እንደዘገበው ወደ 5,000 የሚጠጉ ደቡብ ሱዳናውያን ግጭቱን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱ ሲሆን በደቡብ ሱዳን የተባበሩት መንግስታት ልዑክ ዴቪድ ሺረር ግጭቱ በአገሪቱ ሰላም ለምስፈን የሚደረገውን ጥረት እንደሚያስተጓጉል ተናግረዋል።

በዚሁ በሪክ ማቸር ወታደሮች ይዞታ በሆነው ቦታ ላይ በደረሰ ግጭት ምክንያት በፓርክ  የሚኖሩ 5,000 የሚጠጉ ደቡብ ሱዳናውያን ነፍሳቸውን ለማዳን ወደ ኢትዮጵያ ሸሽተዋል።

በደቡብ ሱዳን አልበርድ ያለው ግጭት በአስር ሺ ለሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሲሆን ወደ 3.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ደግሞ አፈናቅሏል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን በኢትዮጵያ ጋምቤላ በሚገኙ የስደተኛ ጣቢያዎች ተጠልለው ይገኛሉ።

በደቡብ ሱዳን የሚገኙ የሙርሌ ጎሳ አባላት ባለፈው ዓመት በተለያዩ ጊዜ በጋምቤላ በሚኖሩ አኝዋኮች ላይ በፈፀሙት ድንበር ዘለል ጥቃት ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ሲሞቱ በርካታ ሕፃናትና ሴቶች ተጠልፈው እንደተወሰዱ መዘገቡ የሚታወስ ነው።