(ኢሳት-ሐምሌ 5/2009) በህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ /ሕወሃት/ የሚመራው አገዛዝ ባለፈው አመት በሀገሪቱ የተቀሰቀሰው አመጽ ዳግም ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል የገባበት ውጥረት አሁንም እንደተባባሰ መሆኑን ነው የኢሳት ምንጮች እየገለጹ ያሉት።
ለዚህ ደግሞ በአማራ፣ በኦሮሚያና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመጽ ቀጥሏል
ወያኔ ሃርነት ትግራይ እመራዋልሁ ከሚለው ህዝብ በተለያዩ ጊዜያት ከመብት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች ቢቀርቡልትም በሰላማዊ መንገድ መልስ ከመስጠት ይልቅ የሀይል እርምጃ መውሰድን አማራጭ አድርጎ ወስዶታል።
ህወሃት ህዝብን የማፈን ተግባሩን አንድም የአጋዚ ወታደሮችን በማሰማራት ሲቀጥልም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በመደንገግ ቀጥሎበታል።ይሄ እርምጃው ግን ብዙም ያስኬድው አይመስልም ይላሉ የኢሳት ምንጮች።
እንደ ምንጮቹ ከሆነ ወያኔ ኢህአዴግ ራሱ የደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሆን አድርጎታል።
እናም ይህንን አዋጅ ለማንሳት ጣር የሆነበት ወያኔ የአዋጁን መነሳት ክልሎች እንዲደግፉለት በማግባባት ላይ እንደሆነ ነው የኢሳት እማኞች ያረጋገጡት።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በዛሬው እትሙ በፊት ገጹ ላይ ያወጣው ሪፖርትም ይህንን የሚያረጋግጥ ነው።በየክልሎቻቸው የተፈጠረው ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ ደረጃ ላይ ስለደረሰ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳ ችግር እንደሌለባቸው የአማራና ኦሮሚያ ክልሎች አስታወቁ የሚለውን ዘገባውን አስነብቧል።
በአገሪቷ አንድ አንድ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ሁከትና ብጥብጥ ተከትሎ በህገ መንግሥቱ መሰረት መስከረም 28 ጀምሮ ተጥሎ የነበረውና ለሁለተኛ ጊዜ ለአራት ወራት እንዲራዘም የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በክልሎቻቸው ደፍርሶ የነበረውን ሰላምና መረጋጋት ወደ ነበረበት መልሶታል። በመሆኑም ከዚህ በኋላ አዋጁ ቢነሳ ችግር እንደሌለባቸው የየክልሎቹ የአስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊዎች አስታውቀዋል ይላል አዲስ ዘመን በእትሙ።
ለህዝቡ ትልቅ ስጋት የሚሆኑ ችግሮች የሉም፤ በክልሎቻችን አስተማማኝ ሰላም ተፈጥሮዋል፣ በተለይ ህዝቡ ከፀጥታ አካሉ ጋር በመተባበር በብዙ ቦታዎች ፀረ-ሰላም ኃይሎች ተጋልጠው ለህግ እንዲቀርቡ አድርጓል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በአብዛኛው ቦታ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ተፈጥሯል አዋጁ ቢንሳም የሚፈጠር ምንም አይነት ችግር የለም ብለዋል ነው ያለው ጽሁፉ፡፡
የኢሳት ምንጮች ግን ይሄ በፍጹም ከእውነት የራቀ ነው።በየክልሎቹ የተቀሰቀሰው የህዝቡ ቁጣ አሁንም ቀጥሏል።
በተለይ ኢህአዴግ ሰሞኑን ያወጣው አዲስ የግብር አዋጅ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የህዝቡ ቁጣ በአዲስ መልክ እንዲያግረሽ ማድረጉንም ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል።