ሐምሌ ፭ ( አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በብስራት ኤፍ ኤም 101.1 ሬዲዮ ጣቢያ ውስጥ ስፖርት አዘጋጅ በመሆን የሚሰራውን ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒን የመስራት ነጻነት በሚጋፋ መልኩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ማህበር የጻፈውን ደብዳቤ ተከትሎ ማህበሩ በአባላቱ ሥም የተቃውሞ መልስ ጽፏል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ማህበር ሰኔ 16 ቀን 2009 ዓ.ም በብስራት ሬዲዮ ጣቢያ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴውን የሚኮንኑ እና ሚዛናዊነት የጎደላቸው ዘገባዎች ቀርበዋል ሲል ጋዜጠኛ መንሱርን ከሶታል። እግር ኳስ ማህበሩ አክሎም በተደጋጋሚ ጊዜያት ከዚህ ምግባሩ ጣቢያው እንዲታቀብ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን በመጥቀስ ጉዳዩን ወደ ሕግ ለማቅረብ በእለቱ የተላለፈው ዘገባ በሲዲ ተገልብጦ እንዲላክለት በደብዳቤ ጠይቋል።
የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በበኩሉ ”ከጋዜጠኝነት ሥነምግባር በእጅጉ ያፈነገጠ እና የፌደሬሽኑን መሰረታዊ አሰራር ስርዓት የሚያናጋ” በማለት ጋዜጠኛው ሕገመንግስታዊ መብቱን በመጠቀም በነጻነት እንዳይዘግብ እግርኳስ ማህበሩ የማሸማቅቅ ስራ ስረቷል ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በጋዜጠኛ መንሱር ላይ የተወሰደበትን የመብት ጥሰት በህገ መንግስቱ አንቀጽ 29 ተራ ቁጥር 3 እና 4 ላይ የመገናኛ ብዙሃን በነጻነት የመዘገብ መብትን እንደሚጋፋና ውንጀላው በማስረጃ ያልተጨበጠ መሆኑን ጠቅሶ ፌደሬሽኑ የስፖርት ጋዜጠኞች በነጻነት እንዳይዘግቡ ለማድረግ ከማሸማቀቅ ድርጊቱ እንዲታቀብ የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ሃምሌ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ባወጣው የአቋም መግለጫ አሳስቧል።
አንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ ኢትዮጵያ ውስጥ ልምድ ካላቸው ጥቂት ጋዜጠኞች መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ማህበር እንደ አብዛሃኞቹ የኢትዮጵያ መስሪያ ቤቶች ከሙያ ይልቅ በድርጅታዊ አሰራር እና በሙስና የተተበተበ መስሪያ ቤት ነው በሚል ይነቀፋል።