የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክት የቤት ግንባታ ተቋራጮች ገንዘባችንን ተቀማን ይላሉ

ሰኔ ፴ ( ሠላሳ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የተንዳሆ ቤቶች ልማት ግንባታ ምዕራፍ ሁለት ታሳተፊ ስራ ተቋራጮች ሰኔ 12 ቀን 2009 ዓም ለተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት፣ ለስኳር ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ ለአቶ አህመድ አብተው በጻፉት ደብዳቤ ከ200 በላይ የስራ ተቋራጮች ለግንባታ ያወጡት ገንዘብ እንዲመለስላቸው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ላሉ ባለስልጣናት ደብዳቤዎችን ቢጽፉም መልስ ሊያገኙ አለመቻላቸውን ጠቅሰዋል።
“254 ስራ ተቋራጮች ፣እንዲሁም ቤተሰቦቻችንና ሠራተኞቻችን ጨምሮ ፣የስኳር ኮርፖሬሽን ገንዘባችን ዘርፏል። የመስራት ሞራላችንንም ገድሎታል ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል።
የድርጅቱ ምንጮች እንደገለጹት‹‹የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በኮርፓሬሽኑ ከሚከናወኑ ፕሮጀክቶች በሙሉ ሙስና የተንሰራፋበት፣ እንደ ሜቴክ ሁሉ በማንም የማይጠየቅ ፣ የውስጥ ኦዲተሮች የአሰራር፣ የግዢና የመንግስት የኮንትራት አስተዳደር መመሪያ በሥራ እንዲውል የድርጅቱ ሃላፊ ሲጠየቁ፣‘ አጥንትና ደማችን የገበርንለት የሞትንለት ልማት መሆኑን አትዘንጉ›’ እያሉ ጄኔራሉ እንደሚያሸማቅቋቸው” ይገልጻሉ።
ባለስልጣኑ ኮርፖሬሽኑ ሳያውቀው ቻይና በመሄድ ለፋብሪካው የማይሆን የማሽኔሪ ዕቃዎችን ገዝተው ሲመጡ፣ እቃዎቹ ባለመግጠማቸው በግዳጅ ወደ በለስ ፕሮጀክት መላካቸውን፣ ለትራንስፖርት ወጪ በሚልም ለህወኃቱ ትራንስ ኩባንያ 170 ሚሊዮን ብር መክፈላቸውን ምንጮች ተናግረዋል።
አሰራሩ በሠራተኞች ስብሰባ ላይ ሲጋለጥ፣ ባለስልጣኑ “የሞትንለትና የደማንለት ልማት ነው” በማለት ጥያቄውን ያቀረቡትን ሰራተኞች ማስፈራራታቸውን ገልጸዋል።በተንዳሆ የሚሰሩ ሠራተኞች በየጊዜው ስለግንባታው የጥራት ደረጃና ለግንባታ የሚውለውን ግብዓት በሚመለከት ያላቸውን ቅሬታ ለውስጥ ኦዲት በምስጢር ሲያሳውቁ መቆየታቸውን ፣ ግንባታዎቹ እንዲቋረጡ የተደረጉት ከጊዜ መዘግየት በተጨማሪ በዚሁ ጥቆማ መሰረት ጭምር መሆኑን የድርጅቱ ሰራተኞች ይገልጻሉ።
የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ከአስሩ የኮርፖሬሽኑ የፋብሪካ ፕሮጀክቶች ሁሉ በቅድሚያ ተጀምሮ ፣ ማምረት ጀምሮ በአጭር ጊዜ በብልሽት ሥራ ያቆመ ድርጅት ነው።