ኢሳት ዜና ሰኔ 29, 2009
በአዲስ አበባ ባለፉት ሁለት ቀናት ከፍተኛ ጎርፍ ባስከተለው ዶፍ ዝናብ 5 ሰዎች መሞታቸውን የአደጋ መከላከል ባለስልጣናት አስታወቁ ።
በከተማዋ በስተደቡብ ጫፍ ላይ አንድን ወንዝ በመሻገር ላይ የነበሩ 4 ሰዎች በጎርፍ መወሰዳቸውን የአዲስ አበባ የእሳት አደጋ መከላከል ቢሮ ቃል አቀባይ አቶ ንጋቱ ማሞ መግለጻቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል ።
የቱርኩ የዜና ወኪል አናዱሉ ከአዲስ አበባ እንደዘገበው እስከሁን የሁለት ሰዎች አስከሬን ሲገኝ አባትና ልጅ በጎርፍ ተወስደው የደረሱበት አልታወቀም ።
በአዲስ አበበ ጃክሮስ አካባቢ አንዲት ሴት ድልድይ ስትሻገር አዳልጧት ወደ ወንዝ በመግባቷ በውሃው መወሰዷንም ለማረጋገጥ ተችሏል ።
በጎርፉ ሳቢያ 7 ሰዎች በተደረገላቸው እገዛ ከሞት ማምለጣቸውም ተዘግቧል ።
በአዲስ አበባ ካለፈው ግንቦት ወዲህ በረዶ ቀላቅሎ የሚጥለው ዝናብ በከተማዋ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑንና በዚህም ሳቢያ ነዋሪዎቿን ለሞት እየዳረገ መሆኑን የአናዱሉስ ዘገባ ያመለክታል ። በዝናቡ ሳቢያ ከፍተኛ ንብረት መውደሙንም ዘገባው ጨምሮ ገልጿል ።