የኩራዝ አንድ የስኳር ፕሮጀክት ምርት ጀመረ ተብሎ መዘገቡን ሰራተኞች አስተባባሉ ።ማኔጂመንቱና ሜቴክ እየተወዛገቡ ነው።

ሰኔ ፳፱ ( ሃያ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ህወኃት በአማራጭነት ያቋቋመው የቴሌቪዥን ጣቢያ ፣ ኢኤንኤን /ENN/ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ “ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውና በአካባቢው ነዋሪዎች ‘ፋብሪካው ሥራ የሚጀምረው በምጽዓት/በፍርድ ቀን ነው፣ ወይም የፋብሪካውን ሥራ መጀመር የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ ነው (ሜቴክም አያውቀውም)’ ሲባል የነበረው የኦሞ-ኩራዝ 1 የስኳር ፋብሪካ ምርት ጀመሮ ፤ በቀን 650 ቶን ስኳር እንደሚያመርት ፣ በተጓዳኝም ከተረፈ ምርቱ ደግሞ ከፋብሪካው ተርፎ ለሌላ የሚተላለፍ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ ፣ በቀጣይም ምርቱን በእጥፍ አሳድጎ 1300 ቶን ስኳር በየቀኑ እንደሚያመርት ዘግቧል።
ዜናውን የሰሙት የፋብሪካው ሠራተኞች ‹‹ በዚህች አገር በህዝብ ሥም የሚቋቋሙ የመገናኛ ብዙሃን ተጠያቂነት የለባቸውምን ? መንግስትስ ህዝብን ደጋግሞ በማታለል/ በመዋሸት ተጠያቂነት የለበትምን ? ከዚህ ሁሉ አልፎ ቢያንስ እኛን እንደሰው አይቆጥርምን?፣ ሲሉ በመጠየቅ፣ ፋብሪካው አሁን የሚገኝበት ደረጃ ወደ ምርት መግባት ቀርቶ ትክክለኛ ለገበያ የሚቀርብ ስኳር በሙከራ ደረጃም ማምረት ያልጀመረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
“የህዝብን ዕይታ ለመቀየርና ስሞታውን አቅጣጫ ለማስቀየር በሜቴክና ኢኤንኤን /ENN/ የተቀናበረ ዝግጅት እንጂ፣ በተጨባጭ አሁን ላይ የተመረተውን ምርት በዓይን እንዳየነው ምርቱ ሂደቱን ያልጨረሰ ፣ቀለሙ ቡኒ፣ የስኳር ቅርጽ ያልያዘ ‹ዱቄት › ነው፡፡ ይህ የፋብሪካው ሠራተኞች ለቅምሻ ሰጥተውን ዱቀቱን ሻይ ውስጥ ጨምረን ቀምሰነዋል፣ ያጣፍጣል፡፡ ግን የስኳር ቅርጽ የለውም እንደ እህል ዱቄት ደቃቅ ነው፤ ከዚህ ውጪ የተመረተ ምርትም የለም ፡፡ ›› በማለት ስለሁኔታወቅ ያለውን እውነት አስረድተዋል፡፡
እነዚህ የውስጥ የመረጃ ምንጮች እንዳሉት ‹‹ ሜቴክ ለፕሮጀክት ጽ/ቤቱ እንኳን ደስ ያላችሁ፣ ፋብሪካችሁን ምርት አስጀምረናልና ተቀበሉን ›› የሚል ደብዳቤ መጻፉን ገልጸው፣ የፋብሪካው ሥራ መሪዎች ግን‹‹ ስለፋብሪካው የኤሌክትሪክ ሥርዓት፣ የተለያዩ ማምረቻ ክፍሎች መቀናበር ፣ የሚካኒካል ክፍሎች በትክክል ለሥራ መዘጋጀታቸውን … በአጠቃላይም ፋብሪካው ትክክለኛ ምርት ለማምረት ብቁ መሆኑን በባለሙያ ሳናረጋግጥ አንቀበልም፣ ያየነው የተጠናቀቀ ምርት የለም›. በሚል ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ፣ በዚህም ምክንያት በፕሮጀክቱ የሥራ መሪዎች አባላት ላይ በሜቴክ የጦር ሹማምንት ማስፈራሪያና ዛቻ እንደደረሰባቸው ፣ ኃላፊዎቹ በዚሁ ሰግተውና ስለጉዳዩ ለማስረዳት ሥራ አስኪያጁ የተወሰኑ የሥራ መሪዎች ጋር አዲስ አበባ ኮርፖሬሽኑ መሥሪያ ቤት መሄዳቸውንና አሁንም እዚያው እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
አዲስ አበባ የሄደው ማኔጅመንት ቡድን ጉዳዩን ለኮርፖሬሽኑ አስረድቶ ላለመቀበል ያቀረበው ምክንያት በኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ተቀባይነት በማግኘቱ፣ ጉዳዩን በጋራ ለኮርፖሬሽኑ የቦርድ ሰባሳቢ ማቅረባቸውንና በቦርዱ ሰብሳቢም ተቀባነት አግኝቶ ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ በቅርብ ውሳኔ ያገኛል በመባላቸው አዲስ አበባ ሆነው ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ሜቴክ ይህን ፕሮጀክት በሚመለከት ባቀረበው ሪፖርት ጠቅላይ ሚ/ሩን ጭምሮ ማሳሳቱንና ጠ/ሚ/ሩም ፋብሪካው በአንድና ሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ማምረት ደረጃ ይገባል ብለው እንዲናገሩ ማስደረጉን ይሁን እንጅ ከስድስት ወራት በሁዋላም ፋብሪካው ስራ አለመጀመሩን
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሰራተኞች ‹‹ ከዓመታት በኋላ ከኩራዝ 1 ፕሮጀክት የተጀመረውና በቻይናዎች የሚገነባው የኦሞ-ኩራዝ 2 ፕሮጀክት የፋብሪካ ተከላ ተጠናቆ በሙከራ ምርት ትክክለኛ ስኳር ያመረተ ቢሆንም፣ ሜቴክ “እኛን ያስወቅሳል” በሚል ወደ ምርት እንዳይገባ የሸንኮራ አገዳ ከፕሮጀክት 1 እንዳያገኝ በማድረግ ተጽዕኖ ማሳደሩን ፣ እንዲሁም በፕሮጀክቱ ማሳ ለምርት የደረሰ ሸንኮራ ባለመኖሩ በቅርብ ሊጀምር እንደማይችል ፣ ይህም በስኳር ፕሮጀክቶች ያለውን የዕቅድ ክፍተት ያመለክታል፡፡›› በማለት ያለውን የአመራርና አሰራር ክፍተትና የሜቴክ ተጽዕኖ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በኦሞ ኩራዝ 1 ፕሪጀክት ፋብሪካው ባለመድረሱ 870 ሔክታር ሸንኮራ አገዳ ለማስወገድ በመገደዱ ፕሮጀክቱ ይህንን ለማስወገድ በሄክታር 50 ሺህ ብር በድምሩ አርባ ሦስት ሚሊዬን አምስት መቶ ሺህ ብር ወጪ ማድረጉን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩል ከዚህ ከኦሞ አንድ ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ ከመኖሪያ ቀዬኣቸው ተፈናቅለው በአንድ አካባቢ እንዲሰፍሩ የተገደዱ የቦዲ ብሄረሰብ አርብቶአደሮች ለኩፍኝ ወረርሽኝ መዳረጋቸውንና በቂ የመድሃኒት አቅርቦት እና ህክምና እጦት ለከፍተኛ ሥቃይ መዳረጋቸውን የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል፡፡