በአዲስ አበባ በደረሰ የጎርፍ አደጋ አምስት ሰዎች ሞቱ። የአባትና ልጅ አስከሬን እስካሁን አልተገኘም።

ሰኔ ፳፱ ( ሃያ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፉት ሁለት ቀናት በተከታታይ የጣለው ከባድ ዝናብ በፈጠረው ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ በአዲስ አበባ አምስት የከተማዋ ነዋሪዎች መሞታቸውን የአደጋ ሰራተኞች አስታወቁ።
የአዲስ አበባ እሳት አደጋ መከላከያ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ንጋቱ ማሞ እንዳሉት ”በመዲናዋ ደቡባዊ አዋሳኝ ላይ የሚገኝውን ወንዝ ለመሻገር በሚሞክሩበት ወቅት አራት ሰዎች በጎርፍ ተወስደዋል።” በተጨማሪም በቦሌ ጃክሮስ አካባቢም አንድ ሴትዮ ድልድይ በሚሻገሩበት ወቅት ወንዝ ውስጥ ወድቀው ሕይወታቸውን ማጣታቸውንም እና ሌሎች ሰባት ሰዎች ደግሞ ለጥቂት ከሞት መትረፋቸውን አቶ ንጋቱ ማሞ አክለው ተናግረዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ የሁለቱ አስከሬን የተገኘ ሲሆን የአንድ አባት እና ልጅ አስከሬን ግን እስካሁን ሊገኝ አለመቻሉን ባለስልጣኑ አስታውቀዋል። ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ በአዲስ አበባ በተደጋጋሚ ከባድ ዝናብ መጣሉን የቀጠለ ሲሆን በከተማዋ ነዋሪዎች ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል።