ሰኔ ፳፱ ( ሃያ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአርሲ ዞን የምትገኘው የበቆጂ ከተማ ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ ሙሉ ለሙሉ በማጣታቸው ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን አስታውቀዋል። በከተማዋ የነበረው ጥንታዊ የውሃ መስመር አገልግሎት መስጠት ካቆመ ረዥም ጊዜያት ሆኖታል። የከተማዋ መስተዳድርም ሆነ የውሃ ልማት ድርጅቱ የነዋሪዎችን የውሃ ችግር ለመፍታት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አይታይም።
አንድ የአካቢው ነዋሪ ”እኛ የምንኖረው ኑሮ ኑሮ አይባልም። የሚጠጣ ውሃ እንኳን በገንዘባችን ማግኘት አልቻልንም። የውሃ ቧንቧዎች ለስሙ ግቢያችን ውስጥ ቆመዋል። የሚመለከተው አካል ረስቶናል።” ሲሉ የሁኔታውን አሳሳቢነት አስረድተዋል። የታዋቂ ሯጮች መፍለቂያ የሆነችው የበቆጂ ከተማ አርሲ ውስጥ ካሉት ሌሎች ከተሞች ጋር ስትነፃፀር በመሰረተ ልማት ረገድ ወደኋላ ቀርታለች።