ሰኔ ፳፰ ( ሃያ ስምንት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በህወሃት የበላይነት በሚዘወረው ኮማንድ ፖስት ትዕዛዝ የተካሄደውን ግምገማ ተከትሎ ስራቸውን የሚለቁ የፖሊስ አዛዦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን ፣ እስካሁን ባለው መረጃ ከ21 በላይ ኮማንደሮች ስራቸውን ለቀዋል።
ትናንት በነበረው ግምገማ በባህርዳር የጣና ክ/ከተማ ሃላፊ ኮ/ር በላይ ደምሴ ፣ የህዳር 11 ክ/ከተማ ሃላፊ ኮማንደር አልምነው አደመ፣ የበላይ ዘለቀ ክፍለከተማ ሃላፊ ኮማንደር ገበያው ዋለ፣ የሽምብጥ ክ/ከተማ ሃላፊ ኮማንደር እሸቱ ካሳሁን፣ የግንቦት20 ክፍለ ከተማ ሃላፊ ኮማንደር ጌታቸው ውድነህ እና የጣና ክፍለ ከተማ የምርመራ ሃላፊ ኢንስፔክተር ጥሩዘር ስራቸውን ለቀዋል።
በክልሉ ፖሊስ ሰራዊት ውስጥ የተፈጠረው አለመረጋጋት እየጨመረ መምጣቱን የሚገልጹት ምንጮች፣ 3 ከፍተኛ ሃላፊዎችም የስራ መልቀቂያ አስገብተዋል። ይሁን እንጅ ጥያቄያቸው ተቀባይነት አላገኘም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በስራ ላይ እያለ ስራ መልቀቅ አትችሉም የሚል መልስ ለብዙ የፖሊስ አመራሮች እየተሰጠ ነው።
አብዛኞቹ ፖሊሶች የሚገመገሙት በክልሉ ከተፈጠረው ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ በክልሉ ተደርገው የነበሩ አድማዎችን መደገፍ፣ ማበረታታት እንዲሁም በአድማው ወቅት ሱቆቻቸውን ከፍተው የነበሩ አንዳንድ ነጋዴዎችን ሲያሸማቅቁ ነበር የሚሉና ሌሎችም በርካታ የግምገማ ነጥቦች መኖራቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ዋና አዛዥን ጨምሮ የተለያዩ የዞን አመራሮች ስራ መልቀቃቸው ይታወሳል። ከሳምንታት በፊት የታሰረው የቲሊሊ ፓሊስ ሀላፊ ኮማንደር አወቀና 3 ፖሊሶችመ በከባድ የግድያ ወንጀል ተከሰዋል። መዝገቡም ልዩ ፋይል በሚል ለባህርዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተልኳል።
በአጠቃላይ ክልሉ ከህወሃት ተጽኖ ነጻ ይውጣ የሚል ጠንካራ አቋም ያላቸው ፖሊሶች ኢላማ መደረጋቸው በክልሉ ውስጥ አለመረጋጋት እንደሚፈጥር ምንጮች እየገለጹ ነው።
በሌላ በኩል በባህርዳር መግቢያና መውጫዎች እና በጎንደር መስመር ከፍተኛ ወታደራዊ ፍተሻ እየተደረገ ነው።
የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት በተለይ እሁድ ዕለት በባህር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ ፈንጅና ተቀጣጣይ ነገር መገኘቱን ተከትሎ በአካባቢው የሚደረገው ቁጥጥርና ፍተሻ የጠበቀ ሲሆን፤ ረቡዕ ሰኔ 28 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት ከማለዳ አንስቶ በጎንደር መስመርና በባህርዳር መግቢያና መውጫና ከፍተኛ ፍተሻ ሲደረግ ውሏል።
ትናንት መሽት ላይ ደግሞ በተለምዶ በግ ተራ አካባቢ የተወሰኑ ሰዎች ታፍነው ተወስደዋል።