ኢሳት ሰኔ 27/2009
አስራ ሶስት የአሜሪካ ግዛቶች ከእንግሊዝ አገዛዝ ነጻ ወጥተው ዩናይት ስቴት ኦፍ አሜሪካን የመሰረቱበት 241ኛው የአሜሪካ የነጻነት ቀን ማክሰኞ እለት በመላው አገሪቱ ተከብሮ ውሏል።
እ.ኤ.አ በ July 4, 1776 የ13 ግዛቶች ተወካዮች በፔንሲልቬንያ ተሰባስበው ነበር። ከእንግሊዝ አገዛዝ ነጻ መውጣታቸውንና እራሳቸውን የቻሉ ሉአላዊ ግዛቶች መሆናቸውንና በዚሁም ቀን ዩናይትድ ስቴት ኦፍ አሜሪካ መመስረቷን አወጁ። ዲክላሬሽን ኦፍ ኢንዲፔንደንስ የተሰኘውንም የአሜሪካን ነጻነት የሚያውጀውን ህግም በዚሁ ቀን አበሰሩ።
በነጻዋ አገር በዚህ ቀን የመንግስት ስራ ዝግ ሆኖ ሲውል በአሉ በተለያዩ ፌስቲቫሎችና የሙዚቃ ድግስ ተከብሮ ሲውል በምሽት የሚደረገው የርችት ትእይንት የበአሉ ዋና ክንውን ነው።
በዚህ በመዲናይቱ ዋሽንግተን ዲሲ ናሽናል ሞል ተብሎ በሚጠራውና ካፒቶል ሂል እስከ ሊንከን መታሰቢያ ድረስ በተንጠለጠለው ሜዳ ላይ የተለያዩ ትእይንቶች ይቀርባሉ። በዚሁ ቦታ የሚደረገው የሰልፍ ትእይንትና የሙዚቃ ድግስ እንዲሁም በምሽት የሚደረገው እጅግ ደማቅ የሆነ የርችት ትእይንት በመላው አገሪቱ የቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት ብዛት ያለው ህዝብ ይከታተላል።
በዚህ ቀን አሜሪካኖች በመጠራራት በአንድ ቤት በመሰብሰብ በቤታቸው ጓሮና በፓርኮች ውስጥ ጥብስ እየጠባበሱ ቀኑን በደስታ ያሳልፋሉ። በአሜሪካ የሚኖሩ ብዙ ኢትዮጵያውያንም ባህሉን በተመሳሳይ አክብረው ይውላሉ።
ይህም ቀን በአፍሪካ በምትገኝ አንዲት አገር ትልቅ ቀን ነው። በሩዋንዳ ቀኑ በሁቱና ቱትሲ ጎሳዎች መካከል የመቶው ቀን የዘር ግጭት አንድ ሚሊዮን ህዝብ ከቀጠፈ በኋላ ደም መፋሰሱ የቆመበት በመሆኑ እንደ ነጻነት ቀን ይከበራል።