ኢሳት ሰኔ 27/2009
ሰኔ 23 ቀን 2009 የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት 5 አርቲስቶችን እና ተባባሪዎች ያላቸውን የሽብርና የወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።
ሴና ሰለሞን፣ ኢፋ ገመቹ፣ ሃይሉ ነጮ፣ አሊያድ በቀለ እና ኤልያስ ክፍሉ የተባሉ አርቲስቶችና በግል ስራ እንደሚተዳደሩ የተገለጹ ቀነኒ ታምሩ እና ሞይቡሊ ምስጋኑ የቀረበባቸው ክስ ሁከትና አመጽ የሚያነሳሱ ዜናዎችን በኦሮምኛና በአማርኛ ቋንቋ አዘጋጅተው በድምጽ በመቅረጽ ማሰራጨታቸው፤ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ስለ አገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ ቃለ-መጠይቅ በማድረግ ማሰራጨታቸው፤ ሁከትና አመጽን የሚያነሳሱና ሙዚቃዎችን በማዘጋጀት ከኦነግ ባንራና ወታደሮች በማቀናበር በዩቲዩብ ላይ በመጫናቸው እንደሆነ የክስ መዝገባቸው አመላክቷል።
አቃቤ ህግ ባቀረበው በዚህ የሽብርና ወንጀል ክስ ተከሳሾቹ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የወጣቶች “ሰገሌ ቄሮ” ድምጽ ዜና አዘጋጆችና ዜና አንባቢዎች በሚል ቡድን ራሳቸውን በማደራጀት ዜና በምዘጋጀት በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገጾች እንዲሰራጩ በማድረግ ህዝብን ለአመጽ በማነሳሳት ስራ ላይ የቆዩ በማለት “የሽብር ድርጅት ውስጥ በመሳተፍና የሽብር ተግባር በማሴር፣ በማዘጋጀትና በማነሳሳት ወንጀል” በሚል መከሰሳቸውን ገልጿል። ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ለሃምሌ 7 ቀን 2009 አ. ም ቀጠሮ መስጠቱን ለማወቅ ተችሏል።