ሰኔ ፳፮ ( ሃያ ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከበየዳና ደባርቅ አካባቢ ተነስተው ዘመነ ወርቅ በተባለው የተከዜ ሰው ሰራሽ ሃይቅ አካባቢ እንዲሰፍሩ የተደረጉት ነዋሪዎች የክልሉ መንግስት ምንም ዓይነት መሰረተ ልማት ሳያሟላ እንድንሰፍር በማድረጉ ከፍተኛ ችግር ላይ ጥሎናል ብለዋል።
በ2008 ዓም. ከ1400 አባወራ በላይ ወደ አካባቢው እንዲሰፍር ቢደረገም በአጎራባች ክልሎች እንደሚካሄደው ሰፈራ የመሰረተ ልማት ተቋማት ሳይገነቡ በደፈናው ወደ ቦታው መወሰዳቸው የይምሰል አሰራር በመሆኑ አብዛኛዎቹ ሰፋሪዎች ሃብትና ንብረታቸውን በመተው አካባቢውን ለቀው ለመሄድ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡
በአካባቢው ምንም ዓይነት ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ከዘጠና በላይ ተማሪዎች ዓመቱን ሙሉ ያለትምህርት ማሳለፋቸው የገዥው መንግስት በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ ግፍ እየፈጸመበት መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ እምነታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተከዜ ሰው ሰራሽ ሐይቅ አካባቢ ምንም ዓይነት ንጹህ የመጠጥ ውሃ ያልተዘጋጀ መሆኑን የሚገለጹት ሰፋሪዎች፣ በድንገተኛም ሆነ በተለያዩ በሽታዎች ለሚጠቁ ታካሚዎች ምንም ዓይነት ህክምና ሊሰጥ የሚችል የጤና ተቋም በአቅራቢያው አለመገኘቱ ብዙዎች በህመም እንዲሰቃዩና አካባቢውን አልምተው እንዳይጠቀሙ ሆን ተብሎ የተሰራባቸው ግፍ መሆኑን ቅሬታ አቅራቢዎች ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
የአካባቢ ጥበቃ ቦታውን ያስረከበ ሲሆንና ማዘጋጃ ቤቱም ቦታውን በፕላኑ መሰረት እንዳስረከበ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢ፣ ከተማዋ ምንም አይነት የኤሌትሪክ አገልግሎት አለማግኘቷ ትልቅ ችግር ፈጥሮባቸዋል።
በከተማዋ ምንም ዓይነት የጸጥታ አስከባሪ ሃይል ባለመኖሩ ለሌባና ዘራፊዎች በመጋለጥ በመማረር ላይ መሆናቸውን የገለጹት የከተማዋ ሃይል አመራር ኃላፊ፣ አንድን ከተማ ለመጠበቅ ይጠቀሙበት የነበረው አንድ መሳሪያ ብቻ መሆኑ ህዝቡ ከሚመጣበት ዘራፊ ለመከላከል የሚያስችል አቅም እንዳይኖረው ሆን ተብሎ የታቀደ እንደሆነ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡