ሳውዲ አረቢያ ህገወጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚወጡበትን ጊዜ ለአንድ ወር አራዘመች

ኢሳት (ሰኔ 23 ፥ 2009)

የኢትዮጵያውን ስደተኞችን በተመለከተ ሳውዲ አረቢያ አስቀምጣ የነበረውን ቀነ-ገደብ በአንድ ወር መራዘሙ ተነገረ።

የሳውዲ አረቢያ መንግስት የመኖሪያና የስራ ፈቃድ የሌላቸውን የሌላ ሃገራት ዜጎች በሚመለከት በ90 ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ የምህረት አዋጅ መደንገጉ ይታወሳል። 

ይህም ቀነ ገደብ ሰኔ 20/2009 አ ም በመጠናቀቁ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ችግር ላይ ይወድቃሉ የሚል ስጋት ነበር።

በሳውዲ አረቢያ ይኖራሉ ከተባሉ ወደ 4 መቶ ሺህ ኢትዮጵያን እስካሁን የወጡት ከ50 ሺህ በታች መሆናቸው ይነገራል።

ይህንኑ ተከትሎም የኢትዮጵያው አገዛዝ ለሳውዲ አረቢያ መንግስት የጊዜ ይራዘምልኝ ተማጽኖ አቅርቦ ነበር።

በዚህም መሰረት የሳውዲ አረቢያ መንግስት ኢትዮጵያውያን በስደተኞች ከሃገሪቱ እንደወጡ የአንድ ወር ተጨማሪ ጊዜ መሰጠቱን ለማወቅ ተችሏል።

በተራዘመው ቀነገደብ መሰረት ሰነድ ወስደው ከሳውዲ አረቢያ ለመውጣት ፈልገው በተለያዩ ምክንያቶች የዘገዩ ኢትዮጵያውያን እድሉን እንዲጠቀሙበት የሳውዲ አረቢያ መንግስት ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን ገልጿል።

የሳውዲ አረቢያ መንግስት ለአንድ ወር ጊዜ ቀነገደቡን ቢያራዝምም አሁንም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው ያለውን አገዛዝ በመቃወም ለመውጣት አለመፈለጋቸውን እየገለጹ ይገኛል።

የተወሰኑትም ከሳውዲ አረቢያ ወደ የመንና ሌሎች ሃገራት መሸሽ መጀመራቸው ሲገለጽ ቆይቷል።

በሳውዲ አረቢያ 111 ሺህ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ፈቃደኛ ናቸው ቢባልም እስከአሁን የተመለሱት 45 ሺህ ብቻ መሆናቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል።

ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ስደተኞች ወደ ሃገራቸው ሲሄዱ ምን እንደሚጠብቃቸው በውል ስለማያውቁ ስደተኞች አለመሆናቸውንም በተለያዩ አከባቢዎች የተቀበሏቸው ሰዎች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።