ኢሳት (ሰኔ 23 ፥ 2009)
ከቀናት በኋላ ለሁሉም የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ይፋ የሚሆነው የቀን ገቢ ግምትና የግብር ክፍያ የደረጃ ምደባ በነጋዴው ውስጥ ቅሬታ እንደፈጠረና ውስጥ ለውስጥ ተቃውሞ እየቀሰቀሰ መሆኑን በከተማዋ የሚገኙ የኢሳት ምንጮች ገለጹ። በተጨማሪም የችርቻሮ ሱቆችን እስከ ማዘጋት እንደሚደርስ ነጋዴዎቹ አስጠንቅቀዋል ።
መርካቶ ፣ፒያሳ ፣ቂርቆስ ገበያን ጨምሮ በተለያዩ የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች በመዟዟር መረጃ ያሰባሰቡት የአዲስ አበባ የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ በአጭር ቀናት ውስጥ የተካሄደውና ግንቦት 30 ቀን 2009 አ ም እንደተጠናቀቀ ይፋ የተደረገው የቀን ገቢ ግምትና የነጋዴዎች የግብር ክፍያ የደረጃ ምደባ የጎዳና ኮንቴይነር ሱቆችን ጨምሮ ዝቅተኛና መካከለኛ የችርቻሮ ሱቆችን እስከ ማዘጋት እንደሚደርስ ነጋዴዎቹ አስጠንቅቀዋል ።
በአራት ኪሎ ዙሪያ በአስፋልት ዳር የሚገኙትን ትናንሽ የኮንቴይነር ችርቻሮ ሱቆችን በመዞር መረጃ ያሰባሰበው የኢሳት ምንጭ እንደገለጸው ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር ሱቅ በሆኑትና ነጋዴው ከውጭ ቆሞ የሚሸጥባቸው የኮንቴነር ሱቆች አመታዊ የሽያጭ ስሌታቸው ከ200 ሺህ ብር በላይ ተደርጎ በገቢ ገማች ኮሚቴው በተሳሳተ መረጃ መሰላቱን አስታውቀዋል ።ይህም በአዲሱ የቀን ገቢ ግምት ስሌት መሰረት የመካከለኛና ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጎራ እንዲመደቡ እንደሚያደርጋቸው ስጋታቸውን ገልጸዋል ።
በሌላ በኩል የኢህአዴግና ፎረም አባል የሆኑ ከገቢ ገማች ኮሚቴው ጋር የዝምድና እና ጥቅም ትስስር የፈጠሩ እንዲሁም ከገቢዎች ሰራተኛ ጋር በጥቅም የተጎዳኙ ነጋዴዎች ሱቃቸውን ዘግተው እንዲጠፉና ዝቅተኛ ግምት እንዲሰራላቸው በመደረጉ በነጋዴዎች መካከል እርስ በእርስ መጠራጠርና በጠላትነት መተያየት እየተፈጠረ መሄዱን ምንጮቻችን ገልጸዋል ።
ከሚያዝያ 17 ቀን 2009 አ ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 28 ቀን 2009 አ ም ድረስ ከ148 ሺህ ነጋዴዎች በላይ የቀን ገቢ ሽያጭ ግምት የተሰራላቸው መሆኑን ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል ።