የደቡብ አሪ ወረዳ መምህራን የተቃውሞ ፊርማ አሰባስበው አስገቡ

ሰኔ ፳፫ ( ሃያ ሦስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ኦሞ ዞን ደቡብ አሪ ወረዳ የሚገኙ መምህራን በመጋቢት ወር ለአባይ ግድብ ማሰሪያ በሚል ያለፈቃዳቸው ከደሞዛቸው ላይ ገንዘብ እንዳይቆረጥባቸው ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ደሞዛቸው ሳይቆረጥባቸው የቆየ ቢሆንም፣ አሁን ግን የአመቱን የስራ ማጠናቀቂያ ተከትሎ መምህራን ስለሚበታተኑ ተቃውሞ አያነሱም በሚል ከሰኔ ወር ደሞዛቸው ላይ 30 በመቶ እንደሚቆረጥባቸው ወረዳው መናገሩን ተከትሎ መምህራን በከፍተኛ ቁጣ ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል።
በወረዳው የሚገኙ ብዙ መምህራን “ያለፈቃዳችን ደሞዛችን እንዳይነካ” የሚል ደብደባ ጽፈው ለወረዳው ምክር ቤት ፣ ለመምህራን ማህበር እና ለአስተዳደር አካላት እንዲሁም ለደቡብ ኦሞ ዞን አስገብተዋል።
የአባይ ግድብ ዋንጫ ደቡብ ኦሞ ዞን መግባቱን ተከትሎ መምህራን የደሞዛቸውን 30 በመቶ እንዲከፍሉ መጋቢት ፣ 2009 ዓም ላይ በቀረበላቸው ጊዜ ተቃውሞ ማቅረባቸውንና የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተከትሎ ደሞዛቸው ሳይቆረጥባቸው ቆይቷል።