የአጋዚ ክ/ጦር በሰሜን ጎንደር መሳሪያ ለማስፈታት ያደረገው ሙከራ ግጭት አስከተለ

ኢሳት (ሰኔ 22 ፥ 2009)

የአጋዚ ክፍለጦር አባላት በሰሜን ጎንደር ወገራ ወረዳ መሳሪያ ለማስፈታት ያደረጉት ሙከራ ወታደራዊ ግጭት አስከተለ።

የአካባቢው ምንጮች እንደገለጹት ሃሙስ ሰኔ 22/2009 በተካሄደ ግጭት 7 የመከላከያ ሰራዊት አባላት ሲገደሉ ሶስት መቁሰላቸው ተመልክቷል።

በነጻነት ሃይሎች በኩል ስለደረሰው ጉዳት የተገለጸ ነገር የለም። 

ሐሙስ ሊነጋጋ ሲል በሰሜን ጎንደር ዞን ወገራ ወረዳ የተንቀሳቀሱት የአጋዚ ክፍለጦር አባላት ስለዘመቻው በቂ መረጃ በነበራቸው የነጻነት ሃይሎች ድንገተኛ ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው መረዳት ተችሏል። ከክፍለ ጦር አባላት ተነጥለው በቁጥር 10 የሚሆኑት የአንድ ጓድ አባላት የደረሰባቸውን ጥቃት ተከትሎ የአጋዚ ተጨማሪ ሃይል ወደ ስፍራው መንቀሳቀሱን የነጻነት ሃይሎቹ ገልጸዋል።

ቀድመው ወደፊት የቀጡትና አከባቢ እያሰሱ በተንቀሳቀሱት 10 የአጋዚ ወታደሮች በተሰነዘረው ድንገተኛ ጥቃት ሰባቱ ወዲያውኑ ሲገደሉ ሶስቱ መቁሰላቸውንም ተመልክቷል።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም የነጻነት ሃይሎች በተበታተነ የደፈጣ ጥቃት በእንቅስቃሴ ውስጥ መሆናቸው ሲገልጹ የአጋዚ ክፍለጦር አባላትም በአካባቢው ተኩስ መክፈታቸውን ተያይዞ የመጣው ዜና ያስረዳል።

የመንግስት ሃይሎች መሳሪያ ለማስፈታትና ጥቃት ለመሰንዘር መዘጋጀታቸውን ኢሳት ምንጮችን በመጥቀስ መዘገቡ ይታወሳል።

የአጋዚ ክፍለ ጦር የሃይል ርምጃ በህዝብ ውስጥ ከፍተኛ ቁጣ እንዳይቀሰቅስና በዚህም የቀደመው ህወሃትን መሰረት ያደረገው ሁኔታ እንዳይከተል አባል የነበሩት ብ/ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና እንዲመሩት ተደርጓል። ሆኖም በዋናነት ሃላፊነቱን የያዙትና ይህንኑ ለክፍለጦች ሲመሩ የቆዩት የህወሃት አባል የነበሩት ብ/ጄኔራል ገ/መድህን በፍቃዱ ወይንም በቅጽል ስማቸው ወዲ ነጮ ናቸው። ብ/ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና የአጋዚ ክፍለ ጦር አዛዥነቱን ከያዙ በኋላ በዚህ ጦር በጎንደር ዘመቻቸው እንዲጠናከር መደረጉ በአማራና በኦሮሞ መካከል ቅራኔን ያስከትላል በሚል የተቀነባበረ ሊሆን እንደሚችል ግምቶች ተንጸባርቀዋል።