ኢሳት (ሰኔ 22 ፥ 2009)
ለስራ ከሃገር ከወጡ የንግድ ም/ቤት ልኡካን አባላት ሰባቱ ምስራቅ አውሮፓ ሩማንያ ውስጥ መቅረታቸው ተዘገበ።
በግንቦት ወር ከ27 የንግድ ም/ቤት ልኡካን ጋር ወደ ቡካሬስት ሩማንያ የተጓዙት ሰባቱ ግለሰቦች ስለቀሩበት ምክንያት የተገለጸ ነገር ባይኖርም ከመካከላቸው አራቱ ወደ ጎረቤት ሃገር ሃንጋሪ ሲሻገሩ ድንበር አካባቢ መያዛቸው ተነግሯል።
በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ፕሬዝዳንት በአቶ ኤልያስ ገነቱ የተሰራውና ባለፈው ግንቦት ወር ወደ ሩማንያ ቡካሬት የተጓዘው ልዕኩ ብዛት 27 እንደነበርም ተመልክቷል። ከተጓዙት ልኡካን 20ዎቹ ቢመለሱም 7ቱ እንደወጡ ቀርተዋል። ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ንግድ ም/ቤት ዋና ጸሃፊ አቶ ጌታቸው ረጋሳ 7ቱ ሰዎች አለመመለሳቸውን አረጋግጠዋል። ሆኖም ቀርተዋል ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ እንደሆነ አመልክተዋል።
ከሰባቱ የንግድ ም/ቤት ልኡካን አራቱ ወደ ጎረቤት ሃገር ሃንገሪ ሲሻገሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ቢገለጽም አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አልታወቀም። ቀሪዎቹ ስላሉበት ሁኔታ የተገለጸ ነገር የለም።
በአንድ ጊዜ 7 ልኡካን አባላት ሲጠፋ የመጀመሪያው እንደሆነ የተገለጸ ቢሆንም በአነስተኛ ቁጥር እየወጡ መቅረት እየተለመደ መምጣቱም ተመልክቷል። የቀድሞ የንግድና የዘርፉ ማህበራት ም/ቤት ፕሬዝዳንት እንዲሁም ጸሃፊና የቦርድ አባላት እንደወጡ ከቀሩ ልኡካን ውስጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን ሪፖርተር በዘገባው አመልክቷል።