ኢሳት (ሰኔ 22 ፥ 2009)
የብሉምበርግ የዜና ወኪል በሲምንቶ ምርት ላይ በኦሮሚያ ተሰማርቶ የነበረው ዳንጎቴ ሲምንቶ ፋብሪካ ከአስተዳደሩ እየደረሰበት ባለው ጫና ምክንያት ፋብሪካውን ዘግቶ ሊወጣ እንደሚችል ዘግቦ ነበር።
የጽ/ቤት ሃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ በሰጡት አስተያየት “የብሉምበርግ የዜና ወኪል የሰራው ዘገባ መሰረታዊ የጋዜጠኝነት የስነ-ምግባር ያልተከተለ የክልሉን መንግስት መልካም ስም ለማጉደፍ ሆን ተብሎ የተሰራ ተራ ፕሮፖጋንዳ ነው” በማለት አጣጥለውታል። አቶ አዲሱ አያይዘው እንደገጹት የብሉምበርግ ፕሮፖጋንዳ ዋነኛ አላማ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ኢቨስትመንትን በአግባቡ እንደማያስተናግድ አስመስሎ ለማቅረብና አስተዳደሩ ችግሮችን ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት ለማደናቀፍ እንደሆነ ተናግረዋል።
እንደዚህ አይነት የፕሮፖጋንዳ ዘመቻዎች ከዚህ በፊት በሃገር ውስጥ የተለያዩ ሚዲያዎች ተሞክረው ስለተጋለጡ ግባቸውን ሳይመቱ ቀርተዋል በማለት የገለጹት አቶ አዲሱ “ከዚህ በፊት በሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ተሞክሮ ያልተሳካን የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በውጭ ሀገር ሚዲያዎች ለማሳካት መሞከር ተቀባይነት የለውም” ሲሉ አመልክተዋል።
የኦሮሚያ የኮሙኒኬሽ ጉዳዮች ሃላፊው ይህን ይበሉ እንጂ ሰሞኑን በአለም አቀፍ ሚዲያዎች መነጋገሪያ የሆነው የናይጄሪያው ባለሃብት አሊኮ ዳንጎቴ መግለጫ ያስደነገጠው የኢህአዴግ ፓርላማ የንግድና ኢንዱስትሪ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ፋብሪካውን በመጎብኘት የሲሚንቶ ፋብሪካው ያቀረባቸውን ችግሮች ከሚመለከተው አካላት ጋር በመነጋገር ለመፍታት ቃል መግባታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።
ኢሳት ያነጋገራቸው የዘርፉ ሙያተኞች እንደገለጹት ከሆነ ዳንጎቴ ከኢትዮጵያ እንደሚወጣ ማስታወቁ የህዉሃት አገዛዙ ለኢንቨስተሮች ዋስትናና ከለላ መስጠት አለመፈለጉን ያሳያል ብለዋል። ይህም አዳዲስ የውጭ ኢንቨስተሮችንም ሆነ በስራ ላይ የተሰማሩትን መጋበዝና ማቆየት ፍላጎቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው ብለዋል።