ቻይና በወንጀል የሚፈለጉ ቻይናውያን ለመቀበልና ወንጀል የፈጸሙ ኢትዮጵያውያንን አሳልፋ ለመስጠት ከኢትዮጵያ ጋር የተደረገውን ስምምነት አጸደቀች

ኢሳት (ሰኔ 20 ፥2009)

ቻይና በወንጀል የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንንና ሌሎችን ለኢትዮጵያ አሳልፋ ለመስጠት እንዲሁም በወንጀል የምትፈልጋቸውን ቻይናውያንና ሌሎችን ከኢትዮጵያ ለመቀበል የተደረሰውን ስምምነት አጸደቀች። 

የቻይና ዜና አገልግሎት ዥንዋ እንደዘገበው የቻይና ብሄራዊ ህዝባዊ ኮንግረስ ቋሚ ኮሚቴ ማክሰኞ ሰኔ 20/2009 ባካሄደው ስብሰባ ኢትዮጵያና አርጀንቲና በወንጀል የሚፈልጓቸውን ግለሰቦች አሳልፎ ለመስጠት የሚያስችለውን ስምምነት መሰረት ቻይና በወንጀል የምትፈልጋቸውን ግለሰቦች አርጀንቲናም ሆኑ ኢትዮጵያ ለቻይና አሳልፈው የመስጠት ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

ኢትዮጵያና ቻይና ይህንን ስምምነት የተፈራረሙት እ/ኤ/አ በግንቦት ወር 2014 ቢሆንም ከቻይና ም/ቤት ስምምነቱ እስከአሁን ባለመጽደቁ በስራ ላይ ሳይውል ቆይቷል። የኢትዮጵያ ፓርላማ ይህንኑ ስምምነት ከወር በፊት ማጽደቁንም ተያይዞ ከወጣው ዘገባ መረዳት ተችሏል።

 

ቻይና ይህ ስምምነት መሰረታዊውን የሃገሯን የህግ መርህ ባልጣሰና የፍርድ ቤቶችን አሰራር መሰረት ባደረገ መልኩ ተፈጻሚ እንደሚሆን ያመለከተች ሲሆን ስምምነቱ የቻይናን ጥቅም ፍላጎት የማይጋፋ እንደሚሆንም አስታውቃለች። በቻይናው የዜና አገልግሎት ዥንዋ ዘገባ መሰረት የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በተለይም ከፍተኛ የህዉሃት ባለስልጣናት ሃብታቸውን የሚያሸሹት ወደ ቻይና ጭምር እንደሆነ ከመግለጹ ጋር ተያይዞ የህጉ ተፈጻሚነት እስከምን ድረስ የሚሉ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ከመንግስት ለውጥ በኋላ የህጉ ተፈጻሚነትስ ምን ይሆናል የሚለው ምላሽ አላገኘም።