ሰኔ ፲፮( አሥራ ስድስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአማራ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን ሥራቸውን በፈቃዳቸው በሚለቁ ፖሊሶችና ሹመኞች ውዝግብ እየታመሰ ነው።
በተለይ ሰሞኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የአቶ ዓለምነው መኮነን አጃቢ በባህር ዳር ግራንድ ሆቴል መገደላቸውን ተከትሎ እስከ ኮማንደር ድረስ ማዕረግ ያላቸው ፖሊሶችና አዛዦች በፈቃዳቸው ከሥራቸው እየለቀቁ ነው።
የምዕራብ ጎጃም ዞን የምርመራ ሀኃፊ የነበረው እና በአሁኑ ወቅት በክልሉ ፓሊስ ኮሚሽን ውስጥ በኮሚሽነር ደረጃ የልዩ ወንጀሎች ምርመራ ሀላፊ ሆኖ ሢሰራ የነበረው ኮማንደር በላይ በትናንትናው ዕለት በራሱ ፈቃድ ከሥራው መሰናበቱን አስታውቋል።
ኮማንደር በላይ ከሥራው የተሰናበተው ከፍተኛ የማዕረግ ዕድገት ሊሰጠው ባለበት ወቅት ነው።
የልዩ ወንጀሎች ምርመራ ክፍል ኃላፊ የነበረው ኮማንደር በላይ የኮሚሽነርነት ማዕረግ የመጣለት ቢሆንም፤ በባህር ዳር እየተካሄደ ባለው ግምገማ ላይ “ይቅርብኝ ፣ አልፈልግም!” በማለት ሥራውን በገዛ ፈቃዱ መልቀቁን በግልጽ አስታውቋል።
የአቶ ዓለምነውን አጃቢ መገደል ተከትሎ በተደረገው ግምገማ ላይ የክልሉ የወንጀል መከላከል ኃላፊ ኮማንደር አሰፋ ስንታየሁ ጠንካራ ትችቶችን ከሰነሰረ በኋላ “ዛሬ ላይ ማን ለማን እንደሚሰራ አይታወቅም፣ እኔም በዚህ ሁኔታ መሥራት አልችልም” በማለት ስራውን በፈቃደኝነቱ የለቀቀው ከሁለት ቀናት በፊት ነበር።
የነጻነት ኃይሎችና ሌሎች የታጠቁ ቡድኖች በክልሉ እየፈጸሙት ያለው ጥቃት ከክልሉም ሆነ ከፌዴራል መንግስቱ ቁጥጥር ውጪ እየሆነ መምጣቱ፣በህወኃትና በብ አዴን ብቻ ሳይሆን በራሳችን መቆም አለብን በሚሉና የህወኃት ተላላኪ በሆኑ የብአዴን አመራሮች መካከል ጭምር ከፍተኛ አለመግባባትንና ውጥረትን ፈጥሯል።
ማን ለማን እንደሚሠራና እንደሚሰልል የማይታወቅበት ደረጃ ላይ በመድረሱም በክልሉ መስተዳድርም ሆነ በብአዴን ውስጥ የእርስበርስ መጠላለፉና መወነጃጀሉ ተባብሶ መቀጠሉ ታውቋል።